የተባበበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጭፍጨፋ ጨምሮ በአራት አገራት ላይ የተወሰዱ የጅምላ ግድያዎችን እንዲያጣራ ሂውማን ራይትስ ወች ጥሪ አቀረበ።

ሰኔ (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እስካሁን ድረስ በገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማጣራት መሰረት ቁጥራቸው ከ400 በላይ የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውንና ከ10 ሽህ በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች በእስርቤት ሰቆቃ ዘግናኝ ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ ሂውማን ራይትስ ወች ለተ መ ድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በሪፓርቱ ገልጿል። የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በፋጣኝ ሁኔታ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲያደርግ ሲል ጥሪውን አቅርቧል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ በቀጠለው ግድያ፣ የጅምላ እስራት፣ አካላዊ ጥቃት፣ ከትውልድ ቦታ ማፈናቀልን የመሳሰሉ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።

ሂውማን ራይትስ ወች በኢትዮጵያ የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ሰለባ በሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ግድያ ላይ የተሳተፉት ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ ሊደረግ እንደሚገባና ገለልተኛ የምርመራ አጣሪ ቡድን ይቋቋም ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እንዲተባበሩ ድርጅቱ ግፊቱን እንዲያደርግ አሳስብዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በባንግላዲሽ፣ ታይላንድና በየመን በሳኡዲ መራሹ ጦር የተፈፀመው እልቂት በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲመረመር ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ለምክር ቤቱ ጠይቋል።