ሰኔ ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ሃረርጌ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ተቃውሞ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ሃረር ከሃረር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በድንጋይ በመዘጋቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ አርፍዷል። አድማ በታኝ ፖሊሶች ከሃረር ወደ ጨለቆ በማምራት እና በህዝቡ ላይ በመተኮስ መንገዱን ቢያስከፍቱትም፣ ተቃውሞው ግን ይህን ዜና እስካጠናከርንበት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ 9 ሰአት ቀጥሎአል።
አንድ የፖሊስ አባልስ በተኮሰው ጥይት ሳብሪና አብደላ የምትባል መንገድ ላይ ሻሂ በመሸጥ የምትተዳደር እና በቅርቡ የ10ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና የወሰደች ወጣት ሴት ልጅ መገደሏ ተቃውሞውን አባብሶታል። የወጣቷን መገደል ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ተቃውሞውን በመንግስት ላይ ማሰማት የጀመረ ሲሆን፣ ተቃውሞው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ከሃረር የተነሳው ፖሊስ አካባቢውን ተቆጣጠሮታል።
ከቀኑ 9 ሰአት ላይ በነበረው የቀብር ስነስርዓት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ በመነሳቱ ፖሊስ በህዝቡ ላይ ጥይት በመተኮስ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ሞክሯል። የፖሊስን እርምጃ ተከትሎ ምን ያክል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ባይቻልም፣ ከትናንት ጀምሮ በርካታ ሰዎች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ ወኪላችን ገልጿል።
በኦሮሞያ የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም በመካሄድ ላይ ነው። ሂማውን ራይትስ ወች በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ ነበር። በመንግስት የተቋቋመው መንግስታዊው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ወደ 173 ዝቅ ያደርገዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የኦሮምያ ተቃውሞ ከመንግስት ችግሮች ጋር በተያያዘ የተነሳ መሆኑን ቢናገሩም፣ በህዝቡ ላይ ለደረሰው እልቂት እስካሁን ድረስ ተጠያቂ የሆነ አንድም የመንግስት ባለስልጣን የለም።