ሰኔ ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብር ወንጀል ተከሶ 7 አመት የተፈረደበት የሰማያዊ ፓርቲ የአርባምንጭ ተጠሪ የአቶ በፈቃዱ አበበ አባት የሆኑት አቶ አበበ አስፋው ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው 1 አመት ከስድስት ወር የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ውሳኔው እንደተላለፈ አዛውንቱ ወደ አርባምንጭ እስር ቤት ተልከዋል።
በፈቃዱ የአርባ ምንጭ ወጣቶችን እየመለመልክ ለአርበኖች ግንቦት7 ትልካለህ በሚል መታሰሩን ኢሳት በወቅቱ ዘግቦ ነበር። በፈቃዱ በታሰረ ማግስት የፌደራል ፖሊሶች ወደ አቶ አስፋው ቤት በመሄድ እርሳቸውንና ሴት ልጃቸውን ወ/ት አየለች አበበን አስረው በመውሰድ አቶ አስፋው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲደረግ፣ ወ/ት አየለች ግን ወደ ማእከላዊ እስር ቤት ተወስዳ ፣ በአሁኑ ሰአት ቀሊንጦ እስር ቤት ትገኛለች።
አቶ አስፋው ህገወጥ መሳሪያ ተገንቶባቸዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ክሳቸውን እንዳይከላከሉ የተለያዩ ተጽኖዎች ሲደረግባቸው ቆይቷል። ፖሊሶች ፍተሻውን በሚያደርጉበት ወቅት ባሻ መንግስቱ፣ ወ/ሮ አዳነች ተካና ወ/ሮ አልማዝ የተባሉ ሶስት የአይን እማኞችን አዘጋጅተው የነበረ ሲሆን፣ የአይን እማኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ በፖሊስ ሲጠየቁ ሶስቱም በአንድ ላይ “ የተባለውን የጦር መሳሪያ ፖሊሶች ይዘው መምጣታቸውንና በእነሱ እጅ ላይ ማየታቸውን፣ በአቶ አስፋው ቤት ግን ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ተደብቆ አላየንም” ብለው በመናገራቸው ፣ ፖሊስ ፍርድ ቤት ሳያቀርባቸው ቀርቷል። አቶ አስፋው ሶስቱ የአይን ምስክሮች ቀርበው እንዲመሰክሩላቸው ደጋግመው ቢጠይቁም፣ ፖሊስ እነሱ ቀርበው መመስከር አይችሉም የሚል ትእዛዝ በማስተላለፉ አቶ አስፋው የመከላከያ ምስክሮችን ማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲያይ ከቆዬ በሁዋላ የፖሊስን ቃል በማመን አቶ አስፋውን ወንጀለኛ ብሎአቸዋል። የአቶ አስፋው ሌላው ልጃቸው በቅርቡ በአርባምንጭ አካባቢ በሚገኝ ጫካ ከመንግስት ሃይሎች ጋር ሲፋለም መገደሉ ታውቋል። ወጣቱ ተጋይ በመንግስት ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ የተበሳጩት የደህንነት ሃይሎች የአቶ አስፋውን አንደኛውን ልጃቸውን ለመያዝ አሰሳ ጀምረዋል። ከአቶ አስፋው ቤተሰብ ጋር የታዩ ሰዎች እየተያዙ በመታሰር ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
መንግስት ከፍተኛ የደህንነት ሃይሉን በአርባምንጭ ከተማ በማሰማራት በርካታ ወጣቶችን በጥርጣሬ ማሰሩን ምንጮች አክለው ተናግረዋል። የአቶ አስፋው ባለቤት ባላቸውን እንዳይጠይቁ የተደረገ ሲሆን፣ የመንግስት ሃይሎች በቤተሰቡ ላይ እየወሰዱት ያለው የበቀል እርምጃ ዘግናኝ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።