በአዲስ አበባ የተቋቋሙ ወደ አራት ሺ የሚሆኑ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የገቡበት አለመታወቁ ተነገረ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 9 ፥ 2008)

በአዲስ አበባ ከተማ ድህነትን ለመቅረፍ ይረዳሉ ተብለው ከተቋቋሙ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል ወደ አራት ሺ የሚጠጉት የገቡበት አለመታወቁን መንግስት ሃሙስ አስታወቀ።

ከእነዚሁ አራት ሺ ተቋማት በተጨማሪ 1ሺ 600 አካባቢ ኢንተርፕራይዞች ባለቤታቸውና አባሎቻቸውን ማግኘት ሳይቻል መቅረቱን በድርጅቶቹ ላይ ቆጠራን ሲያካሄድ የቆየው መንግስታዊ ድርጅት ገልጿል።

ድርጅቱ ወደ አራት ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪን በማድረግ ቆጠራን ሲያካሄድ ቢቆይም በአጠቃላይ ወደ ስድስት ሺ የሚጠጉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገቡበትና ባለቤታቸው ሳይገኝ መቅረቱ ታውቋል።

የከተማዋ አስተዳደር ድህነትን ይቀርፋሉ ብሎ ያቋቋማቸውና ዱካቸው የገባበት ያልታወቀው ድርጅት አብዛኞቹ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስና የካ ክፍለ ከተማ ከ 10 አመት በፊት የተቋቋሙ እንደነበር ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶቹ ቆጠራ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ዱካቸው የገባበት ያልታወቀ ተቋማት ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በአዲስ አበባ ከተማ የጥቅቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ያሲን ገልጸዋል።

ይሁንና፣ ሃላፊው በመንግስት ላይ ስላጋጠመው የገንዘብ ኪሳራና የችግሩ ምክንያት በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በከተማዋ የተገነቡ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን ለማወቅ ባካሄደው ቆጠራ ወደ 100 የሚጠጉት የገቡበት አለመታወቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።