ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2008)
ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንንና ሬዲዮ /ኢሳት/ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ።
ለኢሳት በስጦታ የተበረከቱ መኪናዎች ቁጥር 120 መድረሳቸው የታወቀ ሲሆን፣ አድቦኬሲ ኢትዮጵያ የተባለ የኢትዮጵያውያን ስብስብ ደግሞ በዚህ ሳምንት ወደ 15ሺህ ዶላር የሚጠጋ ስጦታ አበርክቷል።
ኢሳትን በገንዘብ ከማጠናከር በተጨማሪ፣ በአይነት ድጋፍ እንዲደረግ በቀረበው ጥሪ መሰረት ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ለኢሳት የተበረከቱ መኪናዎች ቁጥር 120 ደርሷል።
ከእነዚህም ውስጥ በህመም ላይ ሆነው፣ መኪናቸውን ለኢሳት ያበረከቱት የሒዩስተን ቴክሳት ነዋሪ ይጠቀሳሉ።
ኢሳትን ለማጠናከር በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች በተጨማሪ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ተቋማትና ማህበራት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል። በዚህ ሳምንት አድቦኬሲ ኢትዮጵያ የተባለ የኢትዮጵያውያን ስብስብ 14,700 የኤሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሻገር በሃገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ መንገድ በተለያየ መጠን ድጋፋቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውም ይታወሳል። ከአንድ መቶ የኢትዮጵያ ብር እስከ 200ሺህ የኢትዮጵያ ብር ከሃገር ቤት ድጋፍ ያደረጉ መኖራቸውም ተመልክቷል።