በሆለታ ስፖንጅ ፋብሪካ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ንብረት አወደመ

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2008)

ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘው የሆለታ ከተማ ሃሙስ በአንድ የስፖንጅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ንብረት በቃጠሎ ወደመ።

ምክንያቱ ባልታወቀውና ማለዳ ላይ እንደደረሰ በተነገረው በዚሁ አደጋ በፋብሪካው ማሽን ላይ ከባድ ውድመት ያደረሰ ሲሆን፣ ፖሊስ የቃጠሎውን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ገልጿል።

ለሽያጭ የተዘጋጁ ምርቶች እንዲሁም ጥሬ እቃዎች በእሳት አደጋው የወደሙ ሲሆን፣ በእሳት ቃጠሎው ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች በወቅቱ ሊደርሱ ባለመቻላቸው ጉዳቱ የከፋ ሊሆን መቻሉን የከተማዋ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን በበኩሉ የቦታው እርቀት ለእሳቱ መባባስ አስተዋፅዖ አድርጓል ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

ፖሊስ በበኩሉ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቆ የእሳት ቃጠሎው መነሻ ለማድረግ ልዩ ግብረሃይል ተቋቁሞ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አክሎ ገልጿል።