በኢትዮጵያ ሆስፒታል ለመገንባት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች ማህበራቸው ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድጋፍ በማድረጉ ተቃውሞ አሰሙ

ኢሳት ( ሰኔ 7 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሆስፒታል በመገንባት የህክምና አገልግሎት እንሰጣለን በሚል በሰሜን አሜሪካ የተሰባሰቡ የህክምና ዶክተሮች ማህበራቸው ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ድጋፍ በማድረጉ፣ ከአባላት ተቃውሞ ገጠመው።

ሆስፒታሉ በተያዘው 2016 ስራ ይጀምራል ተብሎ ቃል የተገባ ቢሆን፣ ግንባታ አለመጀመሩም ጥያቄ አስነስቶ ምንም ስራ ሳይሰራ 600 ሺህ ዶላር ወጪ መሆኑንም አባላቱ አወያይቷል።

በቁጥር 250 የሚሆኑ በትውልድ ኢትዮጵያውያን የሆኑትና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የህክምና ዶክተሮች ያቋቋሙት “ኢትዮ-አሜሪካን ዶክተርስ ግሩፕ” ዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት እንዲመረጡ ደግፎ መቆሙ ጥያቄ ያስነሳው ባለፈው ቅዳሜ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

የሃኪሞቹ ቡድን ቅዳሜ ሰኔ 4 ፥ 2008 በዋሽንግተን ባካሄደው የአባላት ስብሰባ ላይ ከኩባንያው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸውን በድምፅ አስደግፈው ለኢሳት ያደረሱት ምንጮች፣ ክካናዳ የመጡ አንድ የህክምና ዶክተር የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው በተለይ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን በእኛ ስም እንዴት ደገፋችሁ ሲሉ ለቦርዱ አባላት ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህ በኢትዮጵያ የህክምና ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚንቀሳቀሰው የሃኪሞች ቡድን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተርነት እንዲመረጡ ድጋፉን በመግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ ውጤታማ ሆነውባቸዋል ያላቸውን ነጥቦች ዘርዝሯል።

ይህንን በመቃወም በስብሰባው ላይ አስተያየት የሰጡትና ከኩባንያው ባለቤቶች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ግርማ መኮንን ያሰባሰበን፣ ሙያና ኢትዮጵያዊነት እንጂ የፖለቲካ አቋም አይደለምና እንዴት በስማችን ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድጋፍ ትሰጣላችሁ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከካናዳ የመጡት ዶ/ር ግርማ መኮንን ላነሱት ጥያቄ ከቦርዱ አባላት በተሰጠው ምላሽ፣ በተሰጠን ስልጣን አድርገነዋል የሚል ሲሆን፣ በሪፈረንደም ማስወሰን ነበረብን ወይ የሚል አስተያየት ታክሎበታል።

የሃኪሞቹ ቡድን በተያዘው አመት እኤአ 2016 ስራ እንደሚጀምር ቃል የተገባ ቢሆንም፣ የተሰጠው መሬት ተወስዶበት ወደ ሌላ ቦታ መመራት ለመዘግየቱ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ሲሆን፣ ሌላ የተሰጠው ቦታም እንዳይወሰድበት ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድጋፍ መስጠቱ አማራጭ የለውም የሚሉ ወገኖች አሉ።

ሆስፒታሉ ስራ ባልጀመረበት ሌላው ቀርቶ የመሰረት ስራ እንኳን ባልተሞከረበት በአሁኑ ወቅት ለስራ ማስኬጃ በሚል 600 ሺ የአሜሪካን ዶላር ወጪ መሆኑና፣ ይህም እስከ 80 በመቶ ለአንድ ሰው ወጪ መሆኑም በስብሰባው ወቅት በአሳሳቢነቱ ተነስቷል።