ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2008)
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ሃሙስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትና ምክትል ፕሬዚደንቱ ከሃላፊነት አነሳ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ደሞዜ ማሜ እና ምክትላቸው አቶ ቦጀ ታደሰ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከአመታት ካገለገሉበት ስልጣን እንዲነሱ መደረጉ ታውቋል።
ሃሙስ በአዳማ ከተማ የተካሄደው የዳኞቹን ከሃላፊነት መነሳትን ተከትሎ አቶ አዲሱ ቀበኔሳ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙ ሲሆን አቶ ሁሴን ዑስማን ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው ተሹመዋል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ግምገማን በማካሄድ በርካታ ሃላፊዎችን ከስልጣን ሲያነሳ መቆየቱ ይታወሳል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ችግሮች በክልሉ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም እና ሌሎች የልማት ፕሮጄክቶችን ለማጠናቀቅ 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማፅደቁን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ምክር ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለዋል ስላላቸው አርሶ አደሮች ዝርዝር መርጃን ባይሰጥም፣ መልሶ የማቋቋም ስራው ግን በአፋጣኝ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጿል።
የክልሉ ምክር ቤት ሃሙስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሌሎች የምክር ቤት አባላት ያላቸው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።
ይሁንና የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባው ስላስተላለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝር መረጃን ሳይሰጥ መቅረቱን ለመረዳት ተችሏል።
ለአምስት ወራት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በቆየው ተቃውሞ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት የተለያዩ ሃገራት ግድያን የፈጸሙ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡና ድርጊቱም ምርመራ እንዲካሄድበት ሲሉ ይፋዊ ጥያቄ አቅርበው የሚገኝ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት ለተፈጸመው ድርጊት ይቅርታን ማቅረባቸው ይታወቃል።