ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ባለስልጣን በአሜሪካን ህገወጥ የቦንድ ሽያጭ በማድረግ የሰበሰበውን 5.8 ሚሊዮን ድላር ለባለድርሻዎቹ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከእነወለዱ እንዲመልስላቸው ተወሰነበት።
የአሜሪካን የቦንድ ሽያጭና ግዥን የሚቆጣጠረው The Securities and Exchange Commission የተባለው ኮሚሽን ባቀረበው ክስ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካን ባልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ የሰበሰበውን 5.8 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ በድምሩ 6.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል መስማማቱን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ይህም ገንዘብ በህገወጥ መንገድ በአሜሪካን ሀገር ከሚኖሩ ከ3,100 ኢትዮጵያውያን የተሰበሰበ ነው ተብሏል።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የታላቁ አባይ ግድብን ለመገንባት በአሜሪካ አገር ያልተመዘገበና ያልተፈቀደ የቦንድ ሽያጭ ሲያደርግ እንደነረ ገልጾ፣ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ድረገጽ እንዲሁም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ለኢትዮጵያውያን ሲያስነግርና ቦንዱንም ሲሸጥ እንደነበር ተመልክቷል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት እስከ 5.8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከ3,100 በአሜሪካ አገር ከሚኖሩ ሰዎች ከ2011 እስከ 2014 በሚመለከተው አካል ሳያስመዘግብ ሲሰበስብ እንደነበር በክሱ ላይ ተመልክቷል።
የአሜርካን ህግ እስከተከተሉ ድረስ የውጭ መንግስታት በአሜርካ አገር ገንዘብ መሰብሰብ እንደሚችሉ የገለጸው ሴክ የተባለው ይኸው የአሜሪካን የቦንድ ሽያጭና ግዥን የሚቆጣጠረው ድርጅት እንደገለጸው፣ በዚህ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎች ትክክለኛ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክቷል። አሁን እንደተደረገው ስምምነት ከሆነ፣ ገንዘባቸውን ከፍለው ቦንድ የገዙ ሰዎች ገንዘባቸውንና ወለዱን ጭምር ያገኛሉ ሲሉ የድርጅቱ የህግ አስፈጻሚ ዳይሬክተር የሆኑት ሽቴፈን ኮህን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ባለስልጣን የአሜሪካን ህግ መጣሱን በማመኑ 5,847,804 እንዲከፍልና፣ 601 ሺ ዶላር በላይ ወለድ ሊከፍል መማማቱን ድርጅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤት በኩል ሲሸጥ የነበረው የመንግስት ቦንድ ሽያጭ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን ለማሰባሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ እገዳ ስለመጣበት የታሰበው ገቢ ሳያስገኝ መቅረቱን ለመረዳት ተችሏል።