ኢሳት (ሰኔ 1 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ በትምህርት ላይ የሚገኙ የሚገኙ ወደ ስድስት ሚሊዮን ህጻናት ትምህርታቸውን ሊስተጓጎል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በወቅታዊ የሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሪፖርትን ያወጣው ድርጅቱ በድርቁ መባባስ የተነሳ ተማሪዎች ለምግብና ለውሃ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልጿል።
እነዚሁ ለከፋ የድርቅ አደጋ ተጋልጠው የሚገኙትና ቁጥራቸው ወደ ስድስት ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱ ህጻናት ተማሪዎች ከችግሩ አስከፊነት በመነሳት ትምህርታቸውን ሊያቁርጡ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ አስፍሯል።
ወደ 20 የሚጠጉ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ አለመቻሉ ታውቋል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል አለም አቀፍ እርዳታ በመገኘት ላይ ቢሆንም፣ ህጻናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተገኘው ድጋፍ ውስጥ የተሰጣቸው ድርሻ ባለመኖሩ ችግሩ በመባባስ ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ትምህርታቸውን በቋሚነት የማይከታተሉ ሲሉ ችግሩ አፋጣኝ ትኩረት ካልተሰጠው ወደስድስት ሚሊዮን የሚደርሱ ህጻናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሙሉ ለሙሉ ሊያቋርጡ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡና ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ በድርቁ አደጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ኣያሳደረ እንደሚገኝ የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።
ድርቁን ለመከላከል ከሚያስፈልገው 1.5 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ የተገኘ ሲሆን፣ እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር መገኘት እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።