ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤይድስ (HIV/AIDS) ምርመራዎችን ለማካሄድ ይረዳሉ ተብለው ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ የተፈጸመባቸው ቁሳቁሶች ህጋዊ እውቅና በሌለው አንድ የቻይና ኩባንያ ወደ ሃገር ውስጥ መግባቱ ጥያቄ አስነሳ።
ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የህክምና ቋቁሶች አጠቃቀሙን የሚያስረዳ መመሪያ የሌላቸው ሆነው ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውም ታውቋል።
ቤጂንግ ዋንቲ ባዮሎጂካል ፋርማሲ በተባለ ኩባንያ ግዢ የተፈጸመባቸው የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ለአጠቃቀም ምቹ ባለመሆናቸው መንግስት ተጨማሪ ስልጠናን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪን እንደሚያደርግ ባለሙያዎችን ዋቢ በማድረግ ከሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ግዥውን ለመፈጸም አቅራቢ ኩባኒያው በኢትዮጵያ በኩልም ሆነ በአለም ጤና ድርጅት የተመዘገበ ስለመሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ቢቀመጡም የቻይናው ኩባንያ በሁለቱም ወገን መስፈርትን ሳያሟላ የህክምና ቁሳቁሶችን እንዲያቀርብ መደረጉ ታውቋል።
ከወራት በፊት የምግብ መድሃኒቶች አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ወደ ስደስት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ የኤችአይቪ ኤይድስ (HIV/AIDS) መመርመሪያ ቁሶችን ወደ ሃገር ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ካስገባ በኋላ ወደ 20ሺ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች ከቁሳቁሶቹ ጋር እንዲግባቡ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱንም ለመረዳት ተችሏል።
መንግስት የህክምና አገልግሎት ቁሳቁሶችን ለመግዛት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪን ያደረገ ሲሆን፣ ለስልጠናው ከፍተኛ ተጨማሪ ገንዘብ መውጣቱን ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
በሁለተኛ ዙር የተገዙት ቁሳቁሶችን በመጀመሪያ ዙር የተፈጸሙ ግድፈቶችን ይቀርፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ዳግም ችግሩን መከሰቱ ጥያቄን አስነስቶ መገኘቱ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በህክምና አገልግሎት ቁሳቁሶች አስመጪነት የተሰማሩ አቶ ዳዊት ገብረእግዚያብሄር ያለአጠቃቀም መመሪያ የገቡትን ቁሳቁሶች አገልግሎት ላይ ለማዋል መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያመጣ መገደዱን ገልፀዋል።
ኩባንያቸው መስፈርትን ሳያሟላ ቀርቷል ተብሎ ከጨረታ መሰናበቱን የሚናገሩት አቶ ዳዊት የጨረታው ሂደት ከጅምሩ ችግሮች የታዩበት እንደነበር አክለው ገልጸዋል።
በ5.5 ሚሊዮን ዶላር (ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ) ጨረታን በማሸነፍ ደረጃውን ያልጠበቀ የህክምና ቁሳቁስ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ላይ ያለው የቻይናው ኩባንያ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ ቁሳቁሶችን አስገብቶ እንደሚያጠናቅቅም ለመረዳት ተችሏል።
መንግስታዊ የምግብ መድሃኒቶች አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ያለመመሪያ አጠቃቀም ወደሃገር ውስጥ የገቡትን የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ለማዋል በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግሉ የራሱ የአጠቃቀም መመሪያዎች በማዘጋጀት ላይ መሆኑ ታውቋል።
ይሁንና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ ሲል እየወሰደ ያለው አካሄድ ተጨማሪ ኪሳራን እያስከተለ መሆኑን ባለሙያዎች አስረድተዋል።