ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2008)
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነጻ የሆነ የህግ ምክርን አግኝተው የሃገሪቱ የህግ-ስርዓት የሚፈቅደውን አማራጭ እንዲመለከቱ ስምምነት መደረሱን ሃሙስ ይፋ ተደረገ።
ይኸው ስምምነት በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉ የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድና በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል መደረሱን የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምክክክሩ በኋላ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ለሁለት ቀን በአዲስ አበባ ቆይታ የነበራቸው ሚኒስትሩ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን በዋና አጀንዳነት አንስተው የተወያዩ ሲሆን፣ በቀጣይ ሊወስዱ በሚችሉ የህግ አማራጮች ዙሪያም ሰፊ ምክክር ማካሄዳቸው ታውቋል።
ከብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር አብረው የተጓዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ረቡዕ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በእስር ቤት ተገኘተው መጎብኘታቸውንና በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸውን የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በሚኒስትሩ ፊሊፕ ሃሞንድ የቀረበን ጥያቄ ተከትሎ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር የተገናኙ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይትን ቢያካሄዱም ባለስልጣናቱ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት እንደተቆጠቡ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የብሪታኒያ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ በሂደት እንደሚከታተልና ያቀረባቸው ሃሳቦች በምን መልኩ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ቀጣይ ውይይቶችን እንደሚያካሄድ አክሎ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሃገሪቱ መንግስት ዜጋውን ከእስር ለማስለቀቅ በቂ እርምጃን አልወሰደም ሲሉ ዳግም ተቃውሞ መክፈታቸው ታውቋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፊሊፕ ሃሞንድ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ከደረሱት ስምምነት ባሻገር ጠንካራ ውሳኔን ያስተላልፋሉ ተብሎ እንደነበር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ ገልጿል።
ሪፕሪቭ የተሰኘውና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን የሚከታተለው ድርጅት ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንዲፈቱ ይፋዊ ጥያቄን ነበረባቸው ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከተደረሱት ስምምነቶች በተጨማሪ በሂደት ለውጦች ሊደረጉ እንደሚገባ አክሎ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምንም አይነት የህግ ምክርን እንዳያገኙ እገዳ ጥሎ መቆየቱ ይታወቃል።
ረቡዕ በአዲስ አበባ የተደረሰውን የሁለቱ ሃገራት ስምምነት ተከትሎ የህግ ባለሙያዎች ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በቋሚነት በመገናኘት የህግ አማራጮች እንደሚያይ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካወጣው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።