ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2008)
በሽብር ወንጀል ተከሰው ለአንድ አመት ያህል በወህኒ ቤት ታስረው የተፈቱት የዞን 9 ጦማሪያን አባላት ከተለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች እንዳይጓዙ በኢትዮጵያ መንግስት የመጓጓዣ ሰነድ መቀማታቸው ተነገረ።
የህግ መምህርና ጦማሪ ዘላለም ክብረት የዞን 9 ጦማሪያን አባላት ባለፈው አመት ያለፍርድ ሂደት ከእስር የመለቀቃቸው ጉዳይ ለፕሬዚደንት ኦባማ የተሰጠ ገጸ-በረከት ነው ካለ በኋላ፣ “በጊዜው ለምን እንደተለቀቅን ስንጠይቅ፣ መልስ የሚሰጠን አጣን” ሲል NPR ለተሰኘው የሬዲዮ ጣቢያ ተናግሯል። የተወሰኑት የዞን 9 ጦማሪያን ኦባማ ወደ አዲስ አበባ ከመሄዳቸው ከሶስት ሳምንት በፊት መለቀቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘግቡት ጋዜጠኞች የአቅም ማነስ ችግር እንደሚታይባቸው፣ የሚታሰሩበትም ምክንያት መንግስት ላይ ትችት ስለሚያቀርቡ ሳይሆን፣ የሙያ ክህሎት ስለሌላቸው፣ እንዲሁም ጋዜጠኞቹ እያደገ ያለው ዴሞክራሲ ከሚችለው በላይ ስነምግባር የጎደላቸው መሆናቸውን አቶ ሃይለማሪያም ዋቢ በማድረግ ሬዲዮ ጣቢያው ዘግቧል። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ፕሬዚደንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን አቅም እንዲገነባ እንዲረዷቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።
ጦማሪና መምህር ዘላለም ክብረት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ወደስራ መመለስ አለመቻሉን ለNPR ተናግሯል። አሜሪካ አገር ቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ የትምህርት እድል ቢያገኝም፣ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት የእሱንና የአራት ጓደኞቹን የጉዞ ሰነድ እንደነጠቃቸው ለማወቅ ተችሏል።
የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን በገዛ አገራችን እስረኛ ሆነናል ያለው ዘላለም ክብረት፣ ተቃዋሚዎችን በቅርበት አስቀምጦ ቁጥጥር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ስልት እንደሆነ ገልጿል።
የፌዴራል ኮሚውኒኬሽን ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የጦማሪያን የጉዞ ሰነድ መወሰዱን አለማወቃቸውን ገልጸው፣ ሆኖም ግን የህግ አስፈጻሚና ኢሚግሬሽን አካላት የሚፈጽሙትን ስህተቶች ለማስተካከል አመታትን ሊወስድ ይችላል ብለዋል። ለዚህም መፍትሄው ተደጋግሞ የሚነገረው “አቅም ግንባታ” ብቻ እንደሆነ ለNPR መናገራቸው ታውቋል።