ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዋሽንተን ዲሲና ሲያትል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2008)

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰት ብርሃኑ ነጋ በአሜሪካ ዋሽንግተን እንዲሁም በሲያትል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ። ለዲፕሎማሲያዊ ስራዎችና ድርጅታዊ ተግባሮች በአውሮፓና በአሜሪካ ቆይታ ማድረጋቸው የተገለጸው ፕሮፌሰት ብርሃኑ ነጋ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኤርትራ ወደ አውሮፓ ከዚያም ወደ አሜሪካ የተሻገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በጥር ወር 2008 ዋሽንግተን ላይ በተጠራ ስብሰባ ያደረጉትን ንግግር አስታውሰው በቃላቸው የተናገሩት በድርጊት መፈጸሙን ገልጸዋል።

“ትግል የምናደርገው ኤርትራ ውስጥ አይደለም፣ በኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር ላይም ብቻ አይደለም” ማለታቸውን ጠቅሰው፣ ኤርትራ ጋር በማይዋሰነው የኢትዮጵያ ግዛት አርባምንጭ ውስጥ በአርበኞች ግንቦት 7 የተፈጸመው ድርጊት የተግባር ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

“በኛ በኩል እያደረገን ያለነውን በቀደመው ስብሰባ ዘርዝሬያለሁ” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም በስርዓቱ ተቋማትና ደጋፊዎች ላይ ማዕቀብ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

እየተካሄደ ባለው ትግል ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን መጣል ቀላል ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ከባዱ ሁኔታ ስርዓቱ ያመሳቀለውን የሃገሪቱን ችግር ማስተካከልና መስመር ማስያዝ በመሆኑ፣ ይኸው ሁኔታ ከወዲሁ ሊጀመር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ እንዲሁም በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተገኙበት ስብሰባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ የተገኘ ሲሆን፣ ለድርጅቱ ማጠናከሪያ በእያንዳንዱ ከተማ እስከ መቶ ሺ ዶላር ድረስ የደርስ ገንዘብ መሰብሰቡ ተመልክቷል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር የውጭ አመራር ሰብሳቢ ዶክተር አዚዝ መሃመድና የድርጅቱ ዲፕሎማሲያዊ ሃላፊ አቶ ነዓምን ዘለቀ በዋሽንግተን ስብሰባ ተሳታፊ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሜሪላንድና ፔንስልቬንያ ሊቀጻጻስ አቡነ ፊሊጶስ የሚደረገው ትግል ለመብትና ለነጻነት የሚደረግ ትግል ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞ፣ እንዲሁም የጋምቤላ መብት ተከራካሪ ተወካዮች ንግግር አድርገዋል።