ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የመንግስት ተወካይ እንዲገኝ አባቶች ወሰኑ። በዚህ ትልቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ላይ ዕምነቱ የማይታወቅ የመንግስት ተወካይ እንዲሳተፍ ጥሪ መቅረቡን በመቃወም ታዋቂ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለፓትሪያርክ እንደራሴ ለመሾም በሚደረገው ውይይት፣ የመንግስት ተወካይ እንዲገኝ ሃሳቡን ያቀረቡት ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የሲኖዶሱ አባላትም ሃሳቡን ተቀብለው ስምምነታቸውን መግለጻቸው የቤተክርስቲያኒቱን ተከታዮች አስደንግጧል።
ከቤተክርስቲያኒቱ ወንጌል ሰባኪያን አንዱ የሆኑንት ዲያቆን ዳንዔል ክብረት እርምጃውን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ዲያቆን ዳንዔል ክብረት “እኛና መንፈስቅዱስ ማለት ሊቀር ነው” በሚል ርዕስ በድረ-ገጻቸው ባሰፈሩትን ተቃውሞ “በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ የመንግስት ተወካይ እንዲገኝ መጋበዙ በአንድ በኩል የቤተክርስቲያኒቱን ልዕልና የሚነካ፣ በሌላ በኩልም ህገ-መንግስቱን የሚጥስ፣ በመጨረሻም ቀኖና ቤተክርስቲያንን የሚያፈርስ ነው” በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
“ከብጹዓን ጳጳሳት በቀር ካህናትና ቆሞሳት እንኳን በማይገቡበት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማኝ ይሁን ኢዓማኒ፣ የሙስሊም ይሁን ክርስቲያን የማይታወቅ የመንግስት ተወካይ እንዲገኝበት መጋበዙ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳይ ነው” ሲሉም ዲያቆን ዳንዔል ገልጸዋል።
“መንግስትስ ቢሆን ምን ሆኖ ነው ተወካይ የሚልከው?” በማለት የጠየቁት ዲያቆን ዳንዔል ክብረት፣ “ህገ-መንግስታችን መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባ በግልፅ እየደነገገ እንዴት አድርጎ ነው በቀኖናዊ ስብሰባ ላይ የሚገኘው?” ዕርምጃው ህገ-መንስቱን ጭምር የሚጻረር መሆኑን አስታውሰው የመንግስት ተወካይ በተገኘበት የተላለፈ ውሳኔ የመንግስት ወይስ የመንፈስ ቅዱስ ሲሉም በአጽንዖት ጠይቋል።
“ዛሬ እንደዋዛ የተከፈተው በር ነገ እንዝጋህ ቢሉት አስቸጋሪ ነው” ሲሉም አሳስበዋል።
ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮችም በማህበራዊ መድረክ ድርጊቱን እያወገዙ ይገኛሉ።