ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2008)
በቅርቡ ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ሆነው አልተገኙም” ተብለው ከዳኝነት ስራቸው የታገዱት የህግ ባለሙያ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደ አምስት የሚጠጉ ከፍተኛ ዳኞች በተለያዩ መድረኮች ህገመንግስቱን የሚጻረር ንግግርን አድርገዋል ሲል ከዳኝነት ስራቸው እንዲታገዱ ከወራት በፊት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ከዳኝነት ስራቸው እንዲነሱ ከተደረጉት መከከል አንደኛው የሆኑት አቶ ግዛቸው ምትኩ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት በቅርቡ ከፌዴራል አቃቤ ህግ ስር ኣንዲጠቃለል ወደተደረገው የፍትህ ሚኒስቴር ጥያቄን ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በድርጊቱ ቅሬታ ኣንዳደረባቸው የተናገሩት የህግ ባለሙያው ክልከላውን በመቃወም ወደሰበር እንደሚሄዱ አስታውቀዋል።
የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ህገመንግስቱን አለመቀበል ፈቃድ እንዲያስከለክል እንደመስፈርት አለመቀመጡን ያስረዱት የህግ ባለሙያው፣ ለስምንት አመታት በዳኝነት ሲያገለግሉ አንድም ጊዜ በስነምግባር ጉድለትን ተጠይቀው እንዳማያውቁ አስረድተዋል።
የህግ ባለሙያው ጠበቃ የሆኑት አቶ ዳማው አስፋው በበኩላቸው አንድ የህገ-መንግስት አንቀፅ እንዲሻሻል ጠይቀሃል በሚል ከዳኝነት የተነሳን ሰው በፍትህ ስራ ውስጥ ገብቶ እንዳይሰራ ፈቃድ መከልከል ተገቢ አለመሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
በደንበኛቸው ላይ የተወሰደው ውሳኔም በህገመንግስቱ አንቀፅ 25 ላይ ለዜጎች እኩልነት የሰጠውን ድንጋጌ የሚቃረንና በዜጎች መካከል ልዩነት መፍጠር ነው ሲሉም ጠበቃው አክለው አስታውቀዋል።
ይህንኑ አቤቱታ ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ጠበቃው አቶ ዳማው በፍትህ ሚኒስቴር የተሰጠው ውሳኔን በታች ፍርድ ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን አውስተዋል።
ከዳኝነት ስራቸው እንዲታገዱ የተደረጉት ዳኞች በ1977 ዓም የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች የግል አስተያየቶችን ሲሰጡ መቆየታቸውንና ህገ-መንግስቱም ኣንዲሻሻል ጥያቄ ማቅረባቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በውሳኔው ማስነበቡ ይታወሳል።
ከዳኝነት እንዲነሱ የተደረጉት ዳኞች በበኩላቸው የሰጡት አስተያየትም ሆነ ያቅረቡት ጥያቄ ህገመንግስቱን መሰረት ያደረገ እንደሆነ በመግለጽ የተወሰደባቸው እርምጃ መቃወማቸውንም ታውቋል።