ሩሲያ ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ እዳ እንድትሰርዝላት ኢትዮጵያ ጠየቀች

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከሩሲያ መንግስት ያለበትን ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ እዳ “የልማት ፕሮጄክቶች” ለማካሄድ በሚል እዳው የሚሰረዝበትን መንገድ እያግባባ መሆኑን የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘገቡ። ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚቀርቡላትን የልማት ፕሮጄክቶች ዝርዝር በመመርመር በቅርቡ ውሳኔን እንደምታስተላለፍ ስፐትኒክ ኒውስ የተሰኘ የሩሲያ ጋዜጣ የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1998 አም ጀምሮ ሩሲያ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚደርስ እዳ ከኢትዮጵያ መንግስት መሰረዟን ያወሳው ጋዜጣው ቀሪውን ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በልማት ፕሮጄክቶች እንዲለወጥ በኢትዮጵያና በሩሲያ መንግስት በኩል ምክክር ሲካሄድ መቆየቱንም አመልክቷል።

በሩሲያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እዳው በምህንድስና ሳይንስ በፈጠራ ቴክኖሎጂ ዘርፎች እንዲለወጥ ሃሳብ ማቅረቡም ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ ባሰበው በዚሁ ዕዳ ለልማት በተሰኘው ፕሮግራም ሩሲያ የራሷ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ ሃገሪቱ የቀረቡ የልማት ፕሮጄክቶችን በመመርመር በቅርቡ ውሳኔን ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግሩም አባይ ሃገራቸው የሩሲያ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ፍላጎት እንዳላት ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በሩሲያ ኩባንያዎች የተገነቡ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች ለመጠገንና መለዋወጫ ዕቃዎችን ለማቅረብ ሩሲያ ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ የሃገሪቱ የጋዝና የነዳጅ ኩባንያዎች በዚሁ ዘርፍ ለመሰማራት በድርድር ላይ መሆናቸው ታውቋል።