የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት ስራቸውን እየለቀቁ ነው

ግንቦት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለስርዓቱ መቀጠል ዋስትና ይሆናሉ ተብለው ከሚታመንባቸው የጸጥታ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የፌደራል ፖሊስ በሰው ሃይል ድርቅ እየተመታ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

የፖሊስ አባላቱ ከሚደርስባቸው አስተዳደራዊ ጭቆና፣ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የተስፋፋው ፍጹም ዘረኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግርና በአጠቃላይ በስርዓቱ ላይ ተስፋ በማጣት ስራቸውን እየለቀቁ በመጥፋት ላይ ናቸው።

የወታደሮቹ መጥፋት ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የጣለው መንግስት፣ በተለያዩ ዙሮች አዳዲስ ወታደሮችን መልምሎ ለማሰልጠን እቅድ ቢይዝም፣ በበቂ መጠን የሚመዘገቡ ወጣቶች በመጥፋታቸው፣ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ምልምሎች ብቻ ለማሰልጠን እየተገደዱ ነው። ምንጮች እንደጠቆሙት፣ የትግራይ ክልል ደህንነት ቢሮ በአገራቀፍ ደረጃ የጠፉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዝርዝር እንዲላክለት የፌደራል ፖሊስ ዋና ጽ/ቤትን የጠየቀ ሲሆን፣ የደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚጠፉ ወታደሮች ለስርዓቱ አደጋ ይፈጥራሉ የሚል ስጋት እንደገባው ምንጮች  አክለው ገልጸዋል። በአብዛኛው በህወሃት ሰዎች በተያዘው ከፍተኛ አመራሩና በአስተዳደር ሰራተኞችና በተራ ፖሊሶች መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት የተፈጠረ ሲሆን፣ አብዛኛው የአስተዳደር ሰራተኞችና ወታደሮች የተቃዋሚዎች ደጋፊዎች መሆናቸውንና ለውጥ ይመጣል ብለው እየጠበቁ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

ብዙዎቹ መውጫው ጠፍቶባቸውና የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው ስርዓቱን በማገልገል ላይ ቢሆንም፣ አጋጣሚው ሲፈጠርላቸው በስርዓቱ ላይ ለማመጽ የመጀመሪያ ይሆናሉ ሲሉ እነዚሁ የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የአመራር አባላት ይናገራሉ። የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች የሚፈጽሙትን ሙስና እና አስተዳደራዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢሳት በሚቀጥለው ሳምንት መግቢያ ላይ ልዩ ዘገባ እንደሚያቀርብ ያስታውቃል።