64 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በሱዳን መታሰራቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

ኢሳት ( ግንቦት 23 ፥ 2008)

የሱዳን መንግስት 64 ኢትዮጵያውን አስሮ እንደሚገኝና ወደ ኢትዮጵያ በግዳጅ ሊመልስ ይችላል ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽንም የታሰሩትን ኢትዮጵያውያንን እንዳይጎበኝ ተከልክሏል ሲል ለሰብዓዊ ሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሚከራከረው ይኸው አለም አቀፍ ድርጅት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሱዳን በግንቦት 2008 ዓም ብቻ ከ 64 ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም 442 ኤርትራውያንን በግዳጅ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርጋለች ሲል ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በሚታየው የመናገርና የፖለቲካ ነጻነት ጉድለት፣ በተቃዋሚ ሃይሎች ላይ በሚወሰደው የእስር፣ የእንግልት፣ እና ፖለቲካዊ የፍርድ ሂደት የተማረሩ ዜጎች አገራቸውን እየለቀቁ ለስደት ተዳርገዋል ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አትቷል።

ከህዳር 2008 ወር ጀምሮ ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በተነሳት ተቃውሞ በመቶዎችን የሚቆጠሩ ተማሪዎችንና ሌሎች ዜጎች በኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች እንደተገደሉ የገለጸው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሱዳንና ሌሎች ወደ ጎረቤት አገሮች ለስደት ተዳርገዋል ሲል በዘገባው አስነብቧል።

ከሶስት ሳምንት በፊት የሱዳን መንግስት ከሊቢያ ጋር በምትዋሰነው ዶንጎላ በምትባለው ከተማ 313 ኤርትራውያንና 64 ኢትዮጵያውያንን በህገወጥ መንገድ በሱዳን ተገኝታችኋል በሚል ክስ ይዞ እንዳሰሯቸው የገለጸው ይኸው ሪፖርት፣ ኤርትራውያን ወደ አገራቸው በግዳጅ ሲመለሱ፣ ኢትዮጵያውያን ግን እስካሁን እንደታሰሩ በዘገባው አስረቷል።

የአለም አቀፍ ህግ፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደሃገራቸው በግዳጅ እንዳይመለሱ ወይም እንዳይባረሩና በመጀመሪያ ጉዳያቸው በአግባቡ በሚመለከተው አካል እንዲታይ ቢደነግግም፣ የሱዳን መንግስት ግን ኤርትራውያንን በግዳጅ መልሷል፥ ኢትዮጵያውያንም አስሯቸው እንደሚገኝና በቅርቡ በግዳጅ ወደአገራቸው ሊመልስ ይችላል ሲል በሪፖርቱ አስነብቧል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በበኩሉ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን ለመጎብኘት ያደረገው ሙከራ በሱዳን መንግስት እምቢተኝነት እንዳልተሳካ ተገልጿል።

ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ በግዳጅ የተመለሱት ስደተኞች በምን ይዞታ ላይ እንደሚገኙ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ክትትል ማድረግ እንዳልቻሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በየአመቱ በሱዳና በግብፅ በኩል አቋርጠው ወደሊቢያ ከዚያም ወደ አውሮፓ ሊሻገሩ እንደሚሞክሩ የገለጸው የሂውማን ራይትስ ሪፖርት፣ የእነዚህ ስደተኞች መዳረሻም የአውሮፓ ህብረት አገሮች እንደሆነ ገልጿል።

ይሁንና በተለይ በግብፅ ሲናይ ባህረሰላጤ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ታፍነው ብዙ ገንዘብ እንደሚጠየቁና ስቃይ እንደሚደርስባቸው በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

ከስቃዩ የተረፉት ደግሞ በጀልባ ሜዲትራንያን ባህር ላይ ሲጓዙ አደጋ ይደርስባቸዋል። ባለፈው ሳምንት በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ በጀልባ ሲጓዙ ከነበሩት ስደተኞች መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑት በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው መሞታቸው መግለጻችን ይታወሳል።

የአውሮፓ ህብረት ወደ አውሮፓ የሚጎርፉ ስደተኞችን ለማስቆም ለስምንት አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች 46 ሚሊዮን ዩሮ ሊሰጥ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የሱዳን መንግስት በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት አካሄድ ትክክለኛና እንደሆነ ገልጾ፣ ለአፈጻጸሙ እንደሚተባበር መግለጹን ሂውማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ ዘግቧል።

 

ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በሱዳን ዳርፉር ግዛት የራሱን ዜጎች ያላከበረ የሱዳን መንግስት የሌላ አገር ስደተኞችን ያከብራል ብሎ እንደማያስብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።