ከ100 በላይ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በማላዊ ታስረው እየተሰቃዩ ነው ተባለ

ኢሳት ( ግንቦት 23 ፥ 2008)

የማላዊ መንግስት ክ100 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሰብዓዊ መብ በጎደለው ሁኔታ አስሮ ይገኛል ያሉ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድርጊት በመቃወም ሃገር አቀፍ የተቃውሞ ዘመቻን ጀመሩ።

በኢትዮጵያውያን ስደተኞች የእስር ቤት አያያዝ ቅሬታቸውን እየገለፁ ያሉት እነዚሁ ድርጅቶች 119 የሚሆኑና ወደማላዊ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሶስት እስር ቤቶች ለመከራ ተዳርገው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ የእስር ቅጣት ቢያጠናቅቁም አሁንም ድረስ ለረጅም ጊዜ ከእስር ቤት ያልወጡ ስደተኞች መኖራቸውን የማላዊ የሰብዓዊመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ዋቢ በማድረግ ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ማከሰኞ ዘግቧል።

በየዕለቱ ለእስር የሚዳረጉ የኢትዮጵያዊ ስደተኞች ቁጥር መኖሩን የገለጹት ድርጅቶቹ 119 የሚሆኑ ስደተኞች ማኡላ፣ ዴድዛ፣ እና ንቺሲ ተብለው በሚጠሩ እስር ቤቶች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ ታውቋል።

የማላዊ የሰብዓዊ መብት ትምህርት ማዕከል ተብሎ በሚጠራ ተቋም ውስጥ ዋና ስራ አስፈጻሚው የሆኑት ቪክቶር ምሃንጎ ሃገራቸው የሌላ ሃገራት ስደተኞችን ወደየሃገራቸው ብትመልስም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ግን ለሁለት አመት ያህል ጊዜ በእስር ቤት በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የማላዊ መንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የበጀት እጥረት መኖሩንና በየዕለቱ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም መጨመርም ለችግሩ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM)ና ሌሎች ተቋማት ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ከእስር ቤት እንዲወጡ ተደርገው ወደ ሌላ መጠለያ ተቋም እንዲሄዱ ጥያቄን ቢያደርጉም የማላዊ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጥያቄውን ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይታወሳል።

በማላዊ በየጊዜው ለእስር የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መዳረሻቸው ደቡብ አፍሪካ እንደሆነ ቢነገርም ማላዊን ጨምሮ የታንዛኒያና የናሚቢያ መንግስታት ስደተኞቹ በህገ-ወጥ በሃገራችን ሲዘዋወሩ ተገኝተዋል በማለት ስደተኞቹን ለእስር እየዳረጉ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።