ግብፅ ከሃያ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ መለሰች

ኢሳት (ግንቦት 23 ፥ 2008)

የግብፅ መንግስት በሃገሪቱ በኩል ወደ ሌላ ሃገር በህገወጥ መንገድ ለመጓዝ ሙከራን አድርገዋል ያላቸውን ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን፣ የሱዳን እንዲሁም የናይጀሪያን ተወላጆችን በግዳጅ ወደ ሃገራቸው መመለሱ ታውቋል።

መቀመጫቸውን በካይሮ ያደረጉ የየሃገራቱ የኤምባሲ ተወካዮች ስደተኞቹን ወደሃገራቸው ለመመለስ ትብብር ያደረጉ ሲሆን፣ 24 የሚሆኑት ስደተኞች በአራት እስር ቤቶች መቆየታቸውን ካይሮ ፖስት ጋዜጣ ማክሰኞ ዘግቧል።

የግብፅ መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ ባለፉት 10 ቀናቶች የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያላቸው 222 ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመግለጽ ስደተኞቹ በግብፅ በኩል ወደ እስራዔል፣ ሊቢያና ጣሊያን ለመጓዝ እቅድ እንደነበራቸው አስታውቀዋል።

በሚያዚያ ወር ብቻ 15 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጨምሮ አራት የሶማሊያና 19 የኤርትራ ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ወደ አስዋን ከተማ ሲገቡ መያዛቸውንም ካይሮ ፖስት በዘገባው አስፍሯል።

የግብፅ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ከጥር ወር ጀምሮ በርካታ የኢትዮጵያና የሌላ ሃገራት ዜጎች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉም ታውቋል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ግብፅና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት መሰደዳቸውን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ የግብጽ መንግስት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች አለም አቀፍ ህጎች የሚፈቅዱትን ከለላና ጥበቃ እንደሚሰጥ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።