ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በጉዞ ላይ የነበሩ 700 ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር መስጠማቸው ተዘገበ

 

ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ በጀልባ ሲጓዙ ከነበሩት ስደተኞች መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑት በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው መሞታቸው ታወቀ። ክስተቱም በፈረንጆች 2016 ዓም ከተከሰቱት የጀልባ መስጠም አደጋዎች ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ሃሙስና አርብ በሜዲትራንያን ባህር በሶስት ጀልባዎች ላይ የመስመጥ አደጋ የደረሰ ሲሆን፣ 13 ሺ የሚጠጉ አፍሪካውያና ሶሪያውያን ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በባህር ላይ ጉዞ እንዳደረጉ ዘጋርድያን የተባለ በእንግሊዝ አገር የሚታተመው ጋዜጣ እሁድ አስነብቧል።

የአደጋው ሙሉ ዝርዝር እስከትናንት ዕሁድ ድረስ ለመገናኛ ብዙሃን ያልተገለጸበት ምክንያት፣ ስለአደጋው ዝርዝር መረጃ ከተለያዩ ቦታዎች መሰብሰብ አስቸጋሪ ሆኖ በመቆየቱ እንደሆነ ዘጋርድያን በዘገባው አመልክቷል። ሆኖም ከ700 ስደተኞች በላይ መሞታቸውን እርግጠኛ እንደሆኑ የተባብሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ቃለ አቀባይ የሆኑት ካርሎታ ሳሚ (Carlotta Sami) ለዚሁ ጋዜጣ ገልጸዋል።

ባለፈው ሚያዚያ ዓመት በሁለት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ሲሄዱ ከነበሩት አፍሪካውያን ስደተኞች 1ሺ 300 የሚሆኑት ሰጥመው መሞታቸውን የጠቀሰው ዘጋርድያን፣ ባለፈው ሳምንት የተከተሰተው የጀልባ መስጠም አደጋ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች ጀልባዎቹ በሰጠሙበት ቦታ በደረሱም ጊዜም፣ ብዛት ያለው የስደተኞች አስከሬን በባህር ላይ ይንሳፈፍ እንደነበርና የተወሰኑት ስደተኞች ግን በህይወት ቢኖሩም እራሳቸውን ስተው እንደማይቀሳቀሱ የጀርመን የነፍስ አድን ሰራተኞች ዋቢ ያደረገው ዘ ጋርዲያን በዜና ሃተታው አስነብቧል። በህይወት የተረፉት ስደተኞች ለጣሊያን የባህር ጦር መርከብ እንደተሰጡ ተነግሯል።

በባህር ሰጥመው ህይወታቸው ካልፈው ስደተኞች መካከል የጥቂት ወራት ብቻ እድሜ ያለው ህጻን እንደሚገኝበት የገለጸው ዘጋርዲያን፣ ሁለት ፍቅረኛሞች እንደተቃቀፉ ሞተው መገኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑትን ካርሎታ ሳሚን (Carlotta Sami) በስልክ እንዳናገራቸው ዘጋርድያን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የአውሮፓ ህብረት ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የሚጎርፉትን ስደተኞች ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ እስካሁን ድረስ ችግሩ እየባሰ እንጂ ሊገታ አለመቻሉን ዘ ጋርድያን ዘግቧል።  ባለፉት አምስት ወራት 46 ሺ ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው ከሊቢያ ወደ ጣሊያን መድረስ እንደቻሉና ይህም ቁጥር አምና በአንድ አመት ወደአውሮፓ ከደረሱትን ስደተኞ ቁጥር ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ ተመልክቷል።

የአውሮፓ ህብረት ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞችን ለማስቆም ለስምንት አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች 46 ሚሊዮን ዩሮ ሊሰጥ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል። ጀርመንን ጨምሮ በ28 የአውሮፓ አምባሳደሮችን ውይይት የተካሄደበት ይህ እቅድ፣ በምንም መልኩ ለህዝብ ይፋ እንዳይሆንና መታወቅ እንደሌለበትም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አብዛኞቹ ስደተኞቹ በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሶሪያና እና ከአፍሪካ ቀንድ የመጡ እንደሆነም ዘጋርዲያን በዘገባው አስፍሯል።