ጠላቶቻችን ወደ ውስጥ ሰርገው በመግባት ሊያዳክሙንና ሊያሽመደምዱን እየሞከሩ ነው ሲል ኢህአዴግ አስታወቀ

ግንቦት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛውን የግንቦት20 በአል በማክበር ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ ለውይይት ባዘጋጀው ሰነዱ ላይ ግንባሩ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቁን አትቷል። ባለፉት 25 አመታት ከፍተኛ ድል በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተመዘገበ ቢሆንም፣ እነዚህን ድሎች የሚቀለብሱ እንዲሁም የአገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥሉ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው ብሎአል።
ኪራይ ሰብሳቢዎችና የኒዮ ሊበራል ሃይሎች ከውጭ ሆነው ከሚያካሂዱት ጥቃት በተጨማሪ ወደ ውስጣችን ሰርገው በመግባት መንግስታችንን ለማዳከምና ለማሽመድመድ እየሞከሩ ነው ያለው ኢህአዴግ፣ “ ‘ማንኛውንም የተቀናቃኝህ ምሽግ ለመያዝ ቀላሉ መንገድ ከውስጥ ነው” እንደሚባለው በውስጣችን የራሳቸውን ወኪሎች በመመልመል፣ በሙስና ሊማረኩ የሚችሉትን በመማረክ ድርጅታችን የተቀደሰ አገራዊ ተልእኮውን እንዳይፈፅም እስከማደናቀፍ ይደርሳሉ” ብሎአል።
ግንባሩ አያይዞም “ ድርጅታችንና በእርሱ የሚመራው ትግል በብዙ መስኮች ከባድ ፈተናዎችና አደጋዎች እየተጋረጡባቸው” በመሆኑ፣ 25ኛውን አመት በአል ጥልቀት ያለውና መሰረታዊ የራስ ምልከታ ለማድረግ መጠቀም አማራጭ የሌለው ሆኖ ተገኝቷል ብሎአል።
ኢህአዴግ ህዝቡ ትእግስቱ እየተሟጠጠ መምጣቱን እና መብቱን ለማስከበር መታገል መጀመሩንም በሰነዱ አሰፍሯል።
ህዝቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠራቀሙ በመጡ ችግሮቻችን እየተማረረም ቢሆን ከእኛ በቀር ችግሩን ሊፈታ የሚችል እንደሌለ በመተማመን ድምፁን ሲሰጥ ቢቆይም፣ ከነቅሬታውም ቢሆን የመረጠን ህዝብ ድክመቶቻችን ከዛሬ ነገ ይሻሻላሉ ብሎ ተስፋ ሲያደርግ ቆይቶ፣ የመሻሻል ሂደታችን የሚያረካው ሆኖ ባልተገኘበት ጊዜ ወደ አመፅ እስከመገፋፋት ደርሷል ብሎአል ኢህአዴግ፡፡
ሃያ አምስተኛውን የብር ኢዮቤልዩ ስናከብር ልናስተካክላቸው የሚገባን ብዙ ድክመቶች፣ ልንፈታቸው የሚገባን በርካታ ችግሮችና ልንሻገራቸው የሚገባን ግዙፍ ፈተናዎች እንዳሉብን ማውቅ አለብን የሚለው ኢህአዴግ በተፋላሚ ሃይሎች መካከል የሚታይ ትንሽ ወይም መለስተኛ የአቅም ጭማሪ ወይም ቅናሽ በከፍተኛ ደረጃ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው እውነታዎች ተፈጥሮአል ብሎአል።
በህሊናዊ ሁኔታው ረገድ ቀላል የማይባል ተለዋዋጭነት እየታየበት መሆኑን ያልካደው ኢህአዴግ፣ የአረቦች ፀደይ በተቀሰቀሰበት ወቅት ከከባድ የዋጋ ግሽበት ጋር እየተፋለመ ሰላሙን ያስጠበቀው ህዝብ፣ ዛሬ የዋጋ ግሽበት በአንድ አሃዝ ደረጃ በተገደበበት ወቅት በልዩ ልዩ ጥያቄዎች ሳቢያ እየተነሳሳ ወደግጭት እየገባ ነው ብሎአል።
“ የቀለም አብዮተኞችን የአመፅ ጥሪ ላለመቀበል ወስኖ የነበረው ህዝብም በራሱ ግብታዊ መነሳሳት ከባድ ውድመት ያስከተሉ ግጭቶች የቀሰቀሰበት” ሁኔታ ተፈጥሯል ያለው ግንባሩ፣ አምና ድምፁን ለኢህአዴግ የሰጠው ህዝብ ዘንድሮ በአንድ አንድ የአገራችን አካባቢዎች ቅሬታውን በሃይል በመግለጽ ከድርጅቱ ጋር የሚፋለምበት ሂደት እየተከሰተ ነው ብሎአል፡፡
መሬት በማሰባሰብ የታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ኃላፊዎችን ህጋዊ ተጠያቂ በማድረግና አዲስ የሊዝ አዋጅ በማውጣት ገትተነው ከቆየን በኋላ ሁሉንም ቀዳዳዎች ባለመድፈናችን ምክንያት እንደገና አገርሽቷል ያለው ግንባሩ፣ በሪል ስቴት ግንባታ እንዲሁም በመንግስት ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚታይ ኪራይ ሰብሳቢነትም ቀላል አለመሆኑን ገልጿል፡፡ “ከኮንትራት እደላ ጀምሮ እስከ መጨረሻው አፈፃፀም ድረስ የሚታየው ኪራይ ሰብሳቢነት ትንሽ የማይባል ብክነት ከማስከተሉም በተጨማሪ በአንድ በኩል ጥራት ያለው የፕሮጀክት አፈፃፀም እንዳይኖር በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ለመሰለው ጥራቱ የተጓደለ የፕሮጀክት አፈፃፀም ከልክ በላይ ወጪ በማስከፈል ኪራይ ሰብሳቢነቱ አገርን በሁለት ስለት የሚገዘግዝ ቢላ ሆኗል ብሎአል፡፡ ከግዥና ከመሳሰሉ ተግባራት አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የሚታየው ችግር፣ በአጠቃላይ ደግሞ እነዚህን በጊዜና በጥራት ባለመፍታት እየተከሰተ ያለው ችግር በርግጥም በስርዓቱ ላይ ከባድ ፈተና ደቅኗል ሲል ያትታል።
ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሩ በኪራይ ሰብሳቢነት በመዘፈቁ ፈተናዎችን ለመዋጋት ችግር እንደፈጠረ ይገልጻል።
“እጅግ አብዛኛው የአመራር ኃይላችን በተለይ የታችኛው አመራር በእጁ በገባው መንግስታዊ ስልጣን ህዝብን ለማገልገል በከፍተኛ የመስዋዕትነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ ቁጥሩ ትንሽ የማይባል የአመራር ሰው ኃይል ደግሞ ስልጣኑን ካለአግባብ እየተጠቀመበት ነው” ብሎአል። ወደ ላይ በተወጣና ከቀጥተኛ የህዝብ ተፅዕኖ በተራቀ ቁጥርም ችግሩ ይበልጥ እየሰፋ ይሄዳል የሚለው ሰነዱ፣ አመራሩ የመንግስት ስልጣንን ካለአግባብ ለመጠቀም ከሚያደርገው ጥረት በላይ ችግሮችን እያዩ ያለመታገልና ወንበርን አስጠብቆ ለማቆየት በሚደረግ ሙከራ ብዙ መልካም አቅሞችን እንዲመክኑ አድርጓል ሲል ይወቅሳል።
በግብር ስወራ፣ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሞኖፖል አቅጣጫን ተከትሎ ሸማቹን በመዝረፍ፣ መሬት በማግበስበስ ወይም ደግሞ የመንግስትን ፕሮጀክቶች ባልተገባ የጥገኛ መረብ ታግዞ ማግኘትና ጥራቱ የተጓደለ የፕሮጀክት አፈፃፀም በማሳየት እንዲሁም ከህጋዊው በጀት በላይ ከመንግስት ገንዘብ በመውሰድና በመሳሰሉት መልክ ዝርፊያው መጧጧፉን ኢህአዴግ ይናገራል።
ኢህአዴግ የአመራር አካሉ እና አንዳንድ አባላት በብዛት በኪራይ ሰብሳቢነት በመግባታቸው ኪራይ ሰብሳቢነት ዋናው ብቻ ሳይሆን ከበፊቱም የሰፋና በተነፃፃሪ የገዘፈ ሆኖ በወጣበት በዚህ ወቅት፣ ስርአታችን ራሱን በራሱ እንዳያርም እንዲሁም በየመስኩ የምናካሄድው ትግል ተፈላጊ ውጤት በጥራትና በተገቢው ጊዜ እንዳያመጣ አድርጎታል ሲል፣ ከ25 አመታት የስልጣን ጊዜ በሁዋላም ግንባሩ ህልውናውን ለማስቀጠል ፈተና እንደሆነበት ግልጽ አድርጓል።
የግንቦት20 በአልን አስመልክቶ ከፍተኛ አመራሩ ለብቻ ባደረገው ዝግ ስብሰባ አመራሩ እርስ በርስ እስከመወነጃጀል ደርሶ እንደነበር ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል።
እንዲሁም ለኢሳት የደረሰው የኢህአዴግ የበአል አከባበር ዝርዝር መረሃ ግብር እንደሚያሳየው፣ በአሉ እስከ ግንቦት30 የሚቀጥል ሲሆን፣ ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ነጋዴዎችና አርሶአደሮች በአሉን እንዲያከብሩ የማጠቃለያ ሰላማዊ ሰልፍም ያደርጋሉ። በዩኒቨርስቲዎች እና በትምህርት ቤቶች ለሚደረጉ ዝግጅቶች የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ስብሰባዎችን ይመራሉ።
በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር የዳባት ወረዳ ህዝብ ግንቦት20ን አናከብርም ብሎአል።
የዞኑ አመራሮች ግንቦት 16-18 ዳባት ከተማ በመሄድ የወረዳዋን ነጋዴዎች ሰብስበው ስለ ኢህአዴግ 25 አመታት ትግል ሊናገሩ ሲሞክሩ ነጋዴዎቹ “ ኢህአዴግን አናውቀውም? ኢህአዴግ ምናችን ነው? 25 አመታት ሲረግጠን የኖረ ድርጅት ነው ፣ ደርግ ሰርቶ በሰጠን መሰብሰቢያ አዳራሽ 25 አመት ስትሰበስቡን አይሰማችሁም? ዳባት ውስጥ ሁሉም ነገር የደርግ ስጦታችን ነው፣ ደርግን አትውቀሱብን፣ ከአሁን በኋላ የናንተ መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄያችን ይመልስልናል ብለን ተስፋ አናደርግም ደግማችሁ ለስብሰባ እንዳትጠሩን እኛም ጊዜ እስኪመጣልን ድረስ ፈጣሪያችን በፆለት እንምናለን እንጅ ኢህአዴን አንማፀንም” በማለት ከስብሰባ አዳራሽ በማስወጣት ስብሰባው ሳይሳካ መቅረቱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።