ኢህአዴግ የመኖሪያ ሰፈሮችን ማፍረሱን ቀጥሏል

ኢሳት (ግንቦት 16 ፥ 2008)

ኢህአዲግ ባለፈው አመት የምርጫ ወቅት ገብቶት የነበረን ቃል በማፍረስ ህጋዊ ይደረጋሉ ያላቸውን የመኖሪያ ሰፈሮችን በማፍረስ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጡ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ እየፈረሱ ያሉ የመኖሪያ ቤቶች ህገወጥ ሆነው የተገኙ ናቸው በማለት እርምጃው ቀጣይ እንደሚሆን አስታውቋል።

ባልፈው ሳምንት የመኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸውና በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ወረገኑ በሚባል አካባቢ የመኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ግንባታቸው ዳግም ክለሳ ይደረግባታል የሚል ተስፋ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስረድትውዋል።

ይሁንና የከተማው አስተዳደር የተወሰኑትን ህጋዊ በማድረግ ከአንድ ሺ በላይ ቤቶችን በክረምት ወቅት ማፍረሱ ተገቢ አለመሆኑን ነዋሪዎቹ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ህጻናት ተማሪዎች ያለትምህርት መቅረታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች ለአመታት ያፈሩትን ንብረት በአፍራሽ ግብረሃይል መውደሙን ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፊት የተገነቡ ቤቶችን ህጋዊ አደርጋለሁ ሲል በግንቦቱ ምርጫ ወቅት ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው ጊዜ በፊት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችም በዚሁ ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

ይሁንና የከተማው አስተዳደር እርምጃ እንዲወሰድባቸው የተደረጉ ከአንድ ሺ በላይ መኖሪያ ቤቶች ህገወጥ ናቸው ሲል ከነዋሪዎች የቀረበን ቅሬታ አስተባብሏል።

በዚሁ ስፍራ ወደ 20ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለበርካታ አመታት ሲኖሩ እንደነበርም የተገለጸ ሲሆን፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ለማስወጣት በተካሄደው የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ፣ በትንሹ 10 ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ሲሆን፣ የተከማዋ ፖሊስ አስተዳደር ግን ስለተገደሉ ሰዎች ቁጥር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

ህገወጥ ናቸው የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረሱ እርምጃ በተለያዩ የከተማና የክልል ከተሞች ቀጣይ እንደሚሆን ተነግሯል።