1.5 ሚሊዮን ዜጎች በጎርፍ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 15 ፥ 2008)

በተያዘው የክረምት ወቅት 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችል የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን አሳሰበ።

የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በጎርፍ አደጋ የሚፈናቀሉ ሰዎች በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ላይ ተጨማሪ ጫናን እየፈጠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ከአንድ ወር በኋላ የሚገባው የዘንድሮው የክረምት ወቅት ከመጠን በላይ ለሆነ ዝናብና የጎርፍ አደጋ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የአደጋ መከላከል ኮሚሽን ሃላፊ ምትኩ ካሳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።

የጎርፍ አደጋውን ለመቋቋም ቅድመ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ያሳሰቡት ሃላፊው በሃምሌና በነሃሴ ወር ብቻ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ከቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

ባለፈው ወር በተለያዩ ከተሞች የገጠር አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 134 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በሃምሌና በነሃሴ ወር ይደርሳል የተባለው የጎርፍ አደጋ ተመሳሳይ አደጋን ያስከትላል ተብሎም ተሰግቷል።

ከ20000 የሚበልጡ ሰዎች በእስካሁኑ የጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ መሆኑን የገለጹት የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው የጎርፍ አደጋው በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስታውሰዋል።

በሃገሪቱ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው የሰዎች መፈናቀልም ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎችን ቁጥር ሊያሳድግ እንደሚችልና በምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረትን እንደሚያመጣ የእርዳታ ተቋማቱ ይገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በሃገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ በአጠቃላይ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው አደጋ እንደ ደረሰበት አመልክቷል።

አማራ፣ አፋር፣ ሃረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ እና የደቡብ ክልል የጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳይ ያደረሰባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ፣ በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከ30ሺ በላይ የቤት እንስሳትም መሞታቸው ታውቋል።

በሃምሌና በነሃሴ ወር ይደርሳል ተብሎ ከተሰጋው የጎርፍ አደጋ ነዋሪዎችን ለመታደግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ሌላ አካባቢ ማዘዋወር እንደሚያስፈልግም የእርዳታ ድርጅቶች አሳስበዋል።