ኢሳት (ግንቦት 15 ፥ 2008)
በደቡብ ክልል ኮኖሶ ወረዳ ከሚገኝ አንድ እስር ቤት ወደ 60 የሚጠጉ እስረኞች ከእስር ቤት ሰብረው ማምለጣቸውን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ እማኞች እስረኞቹ ሰገን ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ በሳምንቱ መገባደጃ አርብ በሃይል ማምለጣቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በኮንሶ ወረዳ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከእስር ቤት ያመለጡ አብዛኞቹ ሰዎችም የዚሁ ሰለባ የነበሩ እንደሆነ ታውቋል።
የእስረኞቹን ማምለጥ ተከትሎ በወረዳዋ ያሉ የመንግስት ታጣቂዎች እስረኞቹን መልሶ ለመያዝ አሰሳ ቢያካሄዱም እስከሰኞ ድረስ የተያዘ ሰው አለምኖሩን እማኞቹ አስታውቀዋል።
በወረዳዋ ተደጋጋሚ አስተዳደራዊ ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱን ያወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅትም የጸጥታ ሃይሎች በስፍራው ቁጥጥር እያደረጉ እንደሚገኝ አክለው አስረድተዋል።
እስረኞቹ ከእስር ቤቱ ሰብረው ባመለጡ ጊዜም የአካባቢው ነዋሪዎች ከለላ መስጠታቸውንና የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር ትብብርን ሲያደርጉ እንደነበር እማኞች አክለው አስታውቀዋል።
በተለያዩ ጊዜያት ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ለእስር የተዳረጉና ከእስር ቤቱ ማምለጥ ያልቻሉ የተወሰኑ እስረኞች በእስር ቤቱ መቅረታቸውን ምንጮች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ከወራት በፊት በጎንደር ከተማ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል በተባሉ እስረኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ20 የሚበልጡ እስረኞች በተኩስ መገደላቸው ይታወሳል።
በዚሁ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ በቅርቡ በአስተዳደራዊ ጥያቄ ምክንያት በተነሳ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን እነዚሁ እማኞች አክለው አስረድተዋል።
የፌዴራልና የክልሎ ባለስልጣናት ነዋሪዎች ሲያነሱ የነበሩት ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ አግኝቷል ቢሉም በወረዳዋ አሁንም ድረስ አለመረጋጋት መኖሩን ለመረዳት ተችሏል። በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃን ከወረዳዋ ሃላፊዎች ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።