ለባለሃብቶች በተሰጡ ሱቆች ዙሪያ በተደጋጋሚ የተነሱት ቅሬታወች ምላሽ አላገኙም፡፡

ግንቦት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለወጣቶችና ስራ አጥ ወገኖች የሚዘጋጁ የመስሪያ ሱቅ ኮንቴይነሮች በባለ ሃብት እጅ በመገኘታቸው ዙሪያ የተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ አለማገኘታቸውን በተለያዩ ከተማዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለኢሳት አስታወቁ፡፡
ንግድ ፍቃድ የሌላቸው ፣በጥቃቅንና ኢንተርፕራይዝ ያልታቀፉ ነዋሪዎች የመስሪያ ሱቅ እየተሰጣቸው የሚሰሩበት ሁኔታ በግልጽ እየታየ የከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት ርምጃ ከመውሰድ መቆጠባቸው አሳዛኝ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ያቀረቡት ነዋሪዎች በተለያዩ የደህንነት አባላት ክትትል፣ ማስፈራራትና ማዋከቡ እየተጠናከረ በመምጣቱ ዝምታን እንዲመርጡ መገደዳቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡
መስተዳደሩ ለሐገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም የተነሱ ጥቆማዎችን በማጥናት ፍትሃዊ እርምጃ መውሰድ ሲገባው “ለምን ጠቆማችሁ?” በሚል ማዋከቡ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የጥቃቅን አሰራሮች አደራጅተን ስራ ፈጥረናል ፤ስራ እንፈጥራለን የሚለው የገዥው መንግስት ከእውነት የራቀ መሆኑን የተናገሩት ሌላው ቅሬታ አቅራቢ በአብዛኛው ተጠቃሚ ስራ አጥ ወጣቱ ሳይሆን የካቢኔ ቤተሰቦችና ለስርዓቱ ያደሩ የመንግስት ሰራተኛ ቤተሰቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጣቱን በስራ የማሳተፍና በጥቃቅን አደራጅቶ ስራ እንዲፈጥር ለማድረግ የተደረገው ጥረት ደካማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሁልጊዜ ቢያለቅሱም እንባቸውን የሚያብስ አንድም አመራር እንዳላገኙ ምሬታቸውን የሚገልጹት ከአረብ አገር ተመላሽ የሆኑት የሁለት ልጆች እናት ፍትህ በየከተሞች ርቋል ይላሉ፡፡
በአረብ ሃገር ተደብድበው እንደተመለሱ የሚያስታውሱት ቅሬታ አቅራቢ ከመጀመሪያው ወደ አረብ ሐገር እንዲሰደዱ ያደረጋቸው ምክንያት በሚኖሩበት አካባቢ የነበሩት አመራሮች በፈጸሙባቸው በደል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከአረብ ሐገር ከተመለሱ በኋላ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት መተዳደሪያ የሚሆን ስራ የሚሰሩበት ኮንቴይነር ቢጠይቁም መፍትሄ ሊያገኙ እንዳልቻሉ በሃዘን ተናግረዋል፡፡
የመንግስት አመራሮች የችግሩን ስፋት በማሳየቴ “በኮሚቴ ይታይልሻል” በማለት ለረዥም ጊዜ እንዳመላለሱዋቸው የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢ በመጨረሻ እንዲሰሩበት የተሰጣቸው ኮንቴይነር ሌላ ግለሰብ የሚጠቀምበት በመሆኑ በሱቁ ከሚሰራበት ሰው ጋር ለማጋጨት ሆን ብለው በደል እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል፡፡
ውጣ ውረዱ በዛብኝ የሚሉት ግለሰቧ፣ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር በመማረር ፓስፖርታቸውን አድሰው ወደ አረብ ሃገር ለመሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በሃዘን አስረድተዋል፡፡