ሰሞኑን በተከሰተው ጎርፍ ከ20ሺ በላይ ሰዎች ቤት አልባ መሆናቸው ተነገረ

ኢሳት (ግንቦት 12 ፥ 2008)

ሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ከፍተኛ ጎርፍ ከ20 ሺ በላይ ሰዎች ቤት አልባ ማድረጉ ተገለጸ።

በእነዚሁ አካባቢዎች ከተከሰተው ከባድ ጎርፍ በኋላም ብዛት ያላቸው ሰዎች ደብዛቸው እንደጠፋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊዎች አክለው ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚናገሩት ወደፊት በተከታታይ የሚጥለው ዝናብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊያፈናቅላቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከረጅም ድርቅ በኋላ የተከሰተው ድንገተኛ ደራሽ ጎርፍ፣ የእርዳታ አሰጣቱን ሂደት እንዳወሳሰበው ተነግሯል። በመሆኑም ድንገተኛና ደራሽ ጎርፍ በድርቅ ለተጠቁ ወገኖች ይሰጥ የነበረን የእርዳታ አሰጣት አገልግሎትን አስተጓጉሎ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊዎች ገልጸዋል። የጎርፍ አደጋው በመሰረተ-ልማቶች ላይ ያደረሰው ጉዳትም ለምግብ ተረጂዎች በወቅቱ ድጋፍ እንዳይደርስ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

“ሰዎች በተለያዩ ክስተቶች ሊጠቁ ይችላሉ፥ አዝመራ ይወድምባቸዋል ፥ ከብቶች ይሞቱባቸዋል፥ እንዲሁም ሁሉንም ነገር በማጣታቸው ችጋር ውስጥ ይወድቃሉ” ሲሉ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች (OCHA) ሃላፊ ፓውል ሃንድሌይ ለአልጀዚራ ተናግረዋል።

ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃቸው ስድስት ወረዳዎች ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውንሚስተር ሃንድሌይ ለአልጀዚራ በሰጡት ቃለምልል ተናግረዋል። በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች አሁን ደግሞ ደራሽ የጎርፍ አደጋ ተመሳሳይ ጉዳት አድርሶባቸዋል ያሉት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች (OCHA) ሃላፊ ፓውል ሃንድሌይ፣ ከዚህ በፊት ሲረዱ የነበሩ አካባቢዎች አሁንም ሌላ እርዳታ አስፈልጓቸዋል ሲሉ የድርቁንና የጎርፉን አስከፊነትና ስፋት ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በተያዘው 2016 የፈረንጆች አም እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በቅርቡ ትንበያ መስጠቱ መዘገባችን ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ጎርፍና እሱን ተከትሎ ከተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከ150 ሰዎች በላይ መሞታቸውን በሃሙስ ዜና መግለጻችን ይታወሳል። በተለይም በኦሮሚያ፣ በአፋርና፣ በደቡብ ክልሎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ፣ በማሳ ላይ የነበረ የአዝመራና መሰረተ-ልማቶች መውደማቸውን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።