የግብፅ መንገደኞች አውሮፕላን ስብርባሪ በሜዲትራኒያን ባህር ተገኘ

ኢሳት ( ግንቦት 12 ፥ 2008)

ሃሙስ ከፈረንሳይ ወደግብፅ በመብረር ላይ እንዳለ በሜዲተራኒያን ባህር ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን ስባሪ ክፍልና የመንገደኞች ንብረት በውሃ ላይ መገኘቱን የግብፅ ባለስልጣናት ገለጹ።

ከተለያዩ ሃገራት በተውጣቱ የነፍስ አድን ሰራተኞች እየተካሄደ ባለው ፍለጋ አንድ የመንገደኞች ሻንጣ፣ ሁለት ወንበሮችና የአውሮፕላኑ ስብርባሪ አካላት መገኘታቸው የግብፅ መከላከላይ ሰራዊት ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።

የአሮፕላኑ እና የመንገደኞች ንብረቱ ከግብጻዊ የአሌክሳንድሪያ ከተማ በ290 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የተገኘ ስሆን፣ በቀጣይም በርካታ ቁሳቁሶች ይገኛሉ ተብሎ ተገምቷል።

የግብፅ ባለስልጣናት 66 መንገደኞችን ይዞ የነበረው አውሮፕላን በሽብር ጥቃት ሳይወድቅ አልቀረም በማለት ሲሆኑ፣ የግሪክ የባህር ሃይል አባላትም አውሮፕላኑ ከመውደቁ በፊት በእሳት ተያይዞ እንደነበር አስታውቀዋል።

በዚሁ አደጋ 15 ዜጎቿን ያጣችው ፈረንሳይ በበኩሏ፣ አውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው አደጋ እየተሰጠ ያለውን መላ ምት ውድቅ በማድረ አፋጣኝ ምርመራ እንዲካሄድ ጥረትን እያደረገች እንደሆነ ገልጻለች።

የተለያዩ አካላት አውሮፕላኑ የሽብር ጥቃት ሳይሆን አልቀረም በሚል ግምት በመስጠት ላይ ቢሆኑም የትኛውም የሽብር አካል ለጥቃቱ ሃላፊነትን እንደሚወስድ አልገለጸም።

ከወራት በፊት በግብጽ ደርሶ በነበረ ተመሳሳይ አደጋ አብዛኞቹ የሩሲያ ዜጎች የሆኑ 224 መንገደኞች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እራሱን እስላማዊ ግዛት ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለበት ሃላፊነትን ወስዷል።

በነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላት በበኩላቸው የአውሮፕላኑን ሁኔታ መዝግቦ የሚያስቀረው መሳሪያ መገኘት የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ እንደሚረዳ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

ይሁንና መሳሪያ መቼ ይገኝ ይሆን የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ የሚገኝ ሲሆን፣ አሜሪካም ምርመራውን ለማገዝ ዘመናዊ የቅኝት አውሮፕላንን ወደስፍራው አሰማርታለች።

የአቬይሽን ባለስልጣናት በበኩላቸው በአውሮፕላኖች ላይ መድረስ የጀመረው አደጋ በመንገደኞች ስነ-ልቦና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ፈጥሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል።