ግንቦት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሃረሪን ክልል በመምራት ላይ ያለው የኢህአዴግ ተለጣፊ ድርጅት የሆነው ሀብሊ ወጣት አባላት በድርጅቱ መሪዎች ላይ ያነሱትን የሙስና ክስና የመልካም አስተዳደር ችግር በፌስቡክ እና በስብሰባዎች ላይ በማጋለጣቸው ተይዘው መታሰራቸውን የክልሉ ወኪላችን ገልጿል።
ወጣቶቹ በሙስና የተጨማለቁ መሪዎች ወርደው ለፍርድ ይቅረቡ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር ይብቃ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የወሰዱትን ገንዘብ ይመልሱ፣ ከስልጣን ወርደውም ለፍርድ ይቀርቡ የሚሉት ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ሰንብተዋል። ለሁለት ቀናት በተደረገው ግምገማ፣ ወጣቶቹ ያነሱዋቸው ጥያቄዎች የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ አብዱላሃዲን ማእከል ያደረጉ ነበሩ። ፕሬዚዳንቱ በውጭ አገራት ከሚኖሩ የክልሉ ዜጎች የተላከውን 80 ሚሊዮን ብር የእርዳታ ገንዘብ ዘርፈዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ እሳቸውም ገንዘቡን መቀበላቸውን አምነው፣ ነገር ግን ገንዘቡን ውጭ ሃገር ሄደው የጠፉት ባለቤታቸው መውሰዳቸውንና እሳቸው ከችግሩ ንጹህ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከውጭ የመጡትም ሆነ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የሊጉ አባላት የፕሬዚዳንቱን ማስተባባያ ያልተቀበሉት ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በህግ ይጠየቁልን የሚል ጠንካራ አቋም አንጸባርቀዋል።
ግምገማውን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱን ተችተዋል የተባሉ እና ለወጣቶቹ መረጃ በመስጠት ተቃውሞውን ያስተባብራሉ እንዲሁም ለፕሬዚዳንቱ ህይወት አደጋ ፈጥረዋል የተባሉት የፕሬዚዳንቱ የግል ጠባቂና አዛዥ አቶ ባህሩ በፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተቃውሞውን ይመራሉ፣ በፌስቡክም የፕሬዚዳንቱን ስም ያጠፋሉ ተብለው በሌሊት እየታደኑ የታሰሩት የሊጉ አባላት ወጣት መረሃ የሱፍ፣ ወጣት ብሂር አብዲ፣ መምህር አብዲ አህመድ ፣ ወጣት አፈንዲ መሃመድ እንዲሁም ወጣት ነይብ ሲሆኑ፣ በመንግስት ላይ ህዝብን በማነሳሳት መንግስት ለመገልበጥ ሙከራ አድረገዋል የሚልና የሽብርተኝነት ክስ ተከፍቶባቸዋል። ግንቦት7 እና 8 የዋለው ፍርድ ቤት በወጣቶቹ ላይ የቀረበውን ክስ ከተመለከተ በሁዋላ ፣ ፖሊስ የማጣራት ስራውን በ20 ቀናት ውስጥ አጠናቆ እንዲያቀርብ ለግንቦት 29 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የወጣቶቹን መታሰር ተከትሎ የሃረሪ ወጣቶች ግንቦት10 ፣ የታሰሩ ጓደኞቻችን ይፈቱ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ይከበር የሚል የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተገኝተው ተቃውሞ አድርገዋል። በፓርቲው ውስጥ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ ሲደረግ የመጀመሪያው መሆኑን የገለጸው ዘጋቢያችን፣ ከህዝቡ የተነሳውን ተቃውሞ ለማብረድና ውጥረቱን ለማርገብ 4 የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላት ከስልጣን እንዲነሱ ተደርጓል ብሎአል።
በሙስና ወንጀል ተገምግመው ከሃላፊነት ከተነሱት መካከል የሃብሊ አባል፣ ስራ አስፈጻሚና የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የሊጉ አባልና የሃረር የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ ያሲን ሁሴን፣ የሊጉ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የትምህርት ቢሮ ም/ል ሃላፊ እና የወጣቶች ሊግ ሊ/መንበር አቶ ሙክታር ሳልህ፣ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪና የአደረጃጀት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ሃሊድ አልዋን ናቸው። አቶ ያሲን ቀደም ብሎ የቀበሌ 10 ጽ/ቤት በሁዋላም የህዝብ ጤና ጣቢያ የነበረውን ቤት ፣ ጤና ጣቢያው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወር በማድረግ እና ቤቱን በ1 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲታደስ በማስደረግ የእርሳቸው የግል መኖሪያ እንዲሆን ማስደረጋቸው ህዝቡን ማስቆጣቱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። የክልሉ ፕሬዚዳንት የቀድሞ ባለቤት ለእርዳታ የተላከውን ገንዘብ ይዘው መጥፋታቸውን ተመለከተ ዘገባም ኢሳት ከአመት በፊት አቅርቦ ነበር።
ሽኩቻው በሃብሊ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአሃብሊና በኦህዴድ መካከል መሆኑንም ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
ውድ ተመልካቾቻችን ህዳር 29 በሃረር ከተማ ለሚከበረው በአል የኢህአዴግ አባል የሆኑት አቶ በላይነህ ተስፋዬ ለእንግዶች ማረፊያ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ 75 ሆቴል ለመገንባት የነጋዴዎችን እና ነዋሪዎችን ቤቶች ማስፈረሳቸውን በቀረበው ዘገባ ላይ፣ 75 ሆቴሎች የሚለው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ተብሎ እንዲታረም እንዲሁም የተፈናቀሉት 30 ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ ቤተሰቦች ሲፈናቀሉ እስከ 300 የሚደርሱ የቤተሰቡ አባላት እንደሚቸገሩ ለመግለጽ እንወዳለን። ዘገባውን እንዲስተካከል ለጠየቁን የኢሳት ቤተሰቦች ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።