ኢሳት ዜና (ግንቦት 11 ፥ 2008)
ህገወጥ የተባሉ ቤቶችን የማፍረሱ እርምጃ ዛሬ ሃሙስ ቀጥሎ በተፈጠረ ግጭት ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
የመኖሪያ ቤታቸው ከፈረሱባቸው ግለሰቦች መካከልም አንደኛው ሁለት የጸጥታ ሃይሎችን በመግደል የራሱን ህይወት እንዳጠፋም የአካባቢው ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር በደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።
የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚናገሩት ነዋሪዎች ወረገኑ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ዝግ ተደርገው እንደሚገኙና አምቡላንሶች ብቻ ወደ አካባቢው እየገቡ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉት እነዚሁ ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሚገኝ ንብረት መውደሙንና በርካታ ሰዎች ያለመጠለያ መቅረታቸውንም አስረድተዋል።
በጸጥታ ሃይሎች ተገድለዋል ከተባሉት 12 ሰዎች በተጨማሪም ቁጥራቸው በትክልል ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት መግባታቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደው ዘመቻ በአፍራሽ ግብረ ሃይሉ ላይ ጥቃትን አድርሰዋል የተባሉ ነዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሃሙስ ገልጿል።
በነዋሪዎች የተያዙ አካባቢዎች ህገወጥ በመሆናቸውም የመኖሪያ ቤቶቹን የማፍረሱ ድርጊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ አሳስቧል።
ይሁንና፣ ፖሊስ በድርጊቱ ስለሞቱም ሆነ በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።