ግንቦት ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል የተባሉትን ቤቶች ለማፍረስ ወደ ወረዳ 12 የተጓዙት አፍራሽ ግብረሃይሎች እና እነሱን የሚያጅቡዋቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የፌደራል ፖሊሶች ከነዋሪዎች ያጋጠማቸውን ሰላማዊ ተቃውሞ፣ በጥይት ለመመለስ በወሰዱት እርምጃ ከ8 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ100 ያላነሱ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ፣ የሟቾቹን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባይቻልም እስካሁን ባደረጉት ማጣራት ከሲቪሉ 8፣ ከወታደሮች ደግሞ 4 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። በወታደሮች ከተገደሉት መካከል ህጻናትና ታዳጊዎች ይገኙበታል።
የቤት ማፍረሱ ዘመቻ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ወደ አካባቢው እንዳይጠጋ እና እቃውንም እንዳያወጣ በፖሊሶች እየተጠበቀ ነው። ከባድ ጉዳት ላይ ነን የሚሉት ነዋሪዎች በዝናብ ወቅት እንዲሁም ፈተና በደረሰበት ሰአት ልጆቻቸው ሜዳ ላይ መውደቃቸው ልባቸውን ሰብሮታል። ኢትዮጵያዊነታችን እያጠራጠረን ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ወጣቱ ግራ ገብቶት እንደሚገኝ ገልጸዋል። “በክረምት መጠለያ ይሰጣል እንጅ ቤት አይፈርስም” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ኢትዮጵያውያን እንዲደርሱላቸው ይማጸናሉ።