ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2008)
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጽ/ቤት የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ በ94 መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሂሳብ መገኘቱን ይፋ አደረገ።
የ2007 የመንግስት መሪያ ቤቶች በጀት አጠቃቀም በተመለከተ ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀረበው ጽ/ቤቱ በመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የሚፈጸሙ የፋይናንስ ጥሰቶች ከአመት አመት እየተባባሰ መምጣቱንም አስታውቋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የምርጫ ቦርድ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ኤርፖርቶች ቅርንጫፍ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸው ታውቋል።
እነዚሁ የፋይናንስ ጥሰት የታየባቸው መንግስታዊ ድርጅቶች ከመመሪያና ደንብ ውጭ ግዢዎችን ሲፈጽሙ መገኘታቸውንና የት እንደገባ ያልታወቀ ገንዘብም እንደተመዘገበባቸው የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
የሰሌዳ ቁጥር ያላቸው በርካታ ተሽከርካሪዎች የገቡበት አለመታወቁን በሪፖርቱ ያወሳው ጽ/ቤቱ በመንግስታዊ ተቋማት ላይ እየተፈጸመ ያለው የበጀት አጠቃቀም ችግር አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን ገልጿል።
የኮንዶሚኒየም ህንጻዎችና የተሽከርካሪ መጥፋቱ ልዩ ትኩረትን እንደሚሻ የተናገሩት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ችግሩ እልባት ካላገኘ ነገ የተገነባ መንገድ ጠፋ የማንባባልበት ምክንያት ላይኖር ነው ወይ ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ የመንግስት ድርጅቶች በየአመቱ የሚሰጣቸውን አስተያየትና ማሳሰቢያ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የሚፈጽሙት የፋይናንስ ጥሰት እየተባባሰ መምጣቱን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት አስረድተዋል።
እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶችና ሃላፊዎች በመኖራቸው ምክንያትም ምክር ቤቱ ጥብቅ ክትትትልና ተገቢውን የጥፋተኝነት እርምጃ እንዲወስድም ሃላፊው ጠይቀዋል።
በመንግስታዊ ድርጅቶቹ ውስጥ ከተገኘው የፋይናንስ ጥሰት በተጨማሪም ጊዜው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች ለህብረተሰቡ እየተሸጡ መሆኑንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ባቀረበው ሪፖርት አስፍሯል።