ግንቦት ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑ በሚባለው ሰፈር በህገወጥ መንገድ ተሰርተዋል የተባሉ ቤቶችን ለማፍረስ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ወደ አካባቢው የሄዱት የአፍራሽ ግብረሃል አባላት እና የፌደራል ፖሊሶች ከነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ያጋጠማቸው ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊሶች ጥይቶችን ወደ ሰዎች በቀጥታ በመተኮሳቸው በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአይን እማኞች እንደሚሉት ወታደሮቹ ህጻናትን ሳይቀሩ ገድለዋል። እስካሁን በደረሰን መረጃ ከ3 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶችም ቆስለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ተይዘው ታስረዋል።
ነዋሪዎች እንደገለጹት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በተወሰደው እርምጃ ህጻናትና ሴቶች ጎዳና ላይ ወድቀዋል። ንብረት ማትረፍ ቀርቶ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እንኳ ለማንሳት አለመቻሉንም ተናግረዋል።
የአፍራሹ ግብረሃይል አባላት ንብረት እየዘረፉ መውሰዳቸውንም ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል። “ድርጊቱ የጫካ ሽፍታ ስራ እንጅ የመንግስት ስራ አይመስልም” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ክረምት እየገባ ባለበት ወቅት የተወሰደው እርምጃ ዘግናኝ ነው በማለት በምሬት ይገልጻሉ።
በፖሊሶች እርምጃ የተገደሉትንም ሆነ የቆሰሉትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ያደረግነው መኩራ አልተሳካም። በመስተዳድሩ በኩልም እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።