ግንቦት ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ትናንት ከሰአት በሁዋላ ከፓርላማ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መልስ ፣ በመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የተገዙ 570 ሚሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጡ መድሃኒቶች ለህዝብ ሳይከፋፈሉ የአግልገሎት ጊዜያቸው አልፎ ወይም ኤክስፓየር አድርጎ በመጋዝኖች ውስጥ መገኘታቸውን አጋልጠዋል። እንዲሁም በግብርና ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች ለአርሶአደሩ መሸጣቸውን ያጋለጡ ሲሆን፣ የአንዳንድ መድሃኒቶች የመጠቀሚያ ጊዜ ካለፈ ከሁለት አመታት በላይ መሆኑን በመግልጽ፣ በአርሶአደሮች ሲቀርቡ የነበረውን አቤቱታ ትክክለኛነት አረጋገጥዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲቲዩት ከተመዘገቡ መኪኖች ውስጥ 10 መኪኖች ሊብሬ ከወጣላቸው በሁዋላ መኪኖቹ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ መጥፋታቸውንም ኦዲተሩ ተናግረዋል።
ማስረጃውን ተከትሎ አንድ የምክር ቤት አባል፣ ሰሞኑን 88 የኮንዶሚኒየም ብሎኮች መጥፋታቸው ተነገረን፤ አሁን ደግሞ 10 ተሽካርካሪዎች ከአንድ መስሪያ ቤት መጥፋታቸው ተገለጸልን፣ ነገ ደግሞ የተገነባው መንገድ ጠፋ ተብሎ እንደማይነገረን ዋስትና የለንም” ብለዋል።
ጄኔራል ኦዲተሩ መስሪያ ቤታቸው በእያመቱ የኦዲት ሪፖርት ቢያቀርብም የሚሰማውና የሚተገብረው ማጣቱን ፣ ሙስናው እየተስፋፋ መምጣቱን ተስፋ በቆረጠ ስሜት አቅርበዋል። የምክር ቤት አባላቱ በሪፖርቱ መደናገጣቸውን ቢናገሩም፣ አጥፊዎቹ ስለሚጠየቁበት ሁኔታ የገለጹት ነገር የለም። ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ስለሜቴክና የስኳር ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም መከላከያ ሚኒስቴር፣ የደህንነት መስሪያ ቤት ስለሚያወጣቸው ወጪዎች ዝርዝር ሪፖርት ማቅረብ ያልቻሉ ሲሆን፣ ይህንም ያላደረጉት የመከላከያ እና የደህንነት መስሪያ ቤት ከፊል ወጪዎች በኦዲተር መስሪያ ቤቱ እንዳይመረመሩ መንግስት መመሪያ በማውጣቱ ነው ተብሏል:: ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በያመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሳይወራረድ መቅረቱን ሪፖርት ያቀርባል።
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሂሳብ መኖሩንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህገወጥ ግዥ ተፈጽሞ መገኘቱን ኢሳት በትናንት ዘገባው ገልጿል። “በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ፣ በአገሪቱ ውስጥ መንግስት የሚባል ተቋም አለ ወይ ያስብላል” ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።