ስራ ላልጀመሩት የስኳር ኮርፖሬሽን ሰራተኞች 160 ሚሊዮን ብር  በላይ ደሞዝ ወጪ ሆኖ እየተከፈለ ነው ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 5 ፥ 2008)

ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦላቸው በስድስት አመት ጊዜ ውስጥ ወደስራ መግባት ያልቻሉ የስኳር ፋብሪካዎች በየወሩ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ለደሞዝ ክፍያ ወጪን እያደረጉ እንደሆነ ተገለጠ።

በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርት ያቀረበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ የስኳር ኮርፖሬሽን የፋብሪካዎች ግንባታ ሳይጠናቀቅ የሰራተኛ ቅጥርን እንዳይፈጽም አሳስቧል።

መንግስት ከተለያዩ አካላት ብድርን በማሰባሰብ የስኳር ፋብሪካዎቹን ለማቋቋም ጥረትን ቢያደርግም፣ ፋብሪካዎቹ ከፍተኛ ኪሳራን እያመጡ እንደሆነ የመንግስት አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይህንኑ ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔን ያስተላለፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ2006 ዓም ጀምሮ ለኦሞ ኩራዝ አንድና በለስ አንድ ስኳር ፋብሪካዎች ብቻ በአመት ለሰራተኛ ደሞዝ ክፍያ 20 ሚሊዮን ብር ሲወጣ መቆየቱን አውስቷል።

የስኳር ኮርፖሬሽን በአጠቃላይ ሊገነቡ ለታሰቡ የስኳር ፋብሪካዎች በየወሩ 160 ሚሊዮን ብር እየከፈለ እንደሆነ ምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

በደሞዝ ክፍያ እየወጣ ካለው ገንዘብ በተጨማሪም ፋብሪካዎቹ ሳይጠናቀቁ ሸንኮራ አገዳ እየተተከለ እንዲቃጠል መደረጉም በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራን እንዳስከተለ የህዝብ ተውካዮች ምክር ቤት በውሳኔው መግለጹን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እንዳወቅ ሃብቴ በበኩላቸው በስራ ተቋራጮች የተሰጠውን ምላሽ መነሻ በማድረግ አገዳ እንዲተከልና ሰራተኞች እንዲቀጠሩ መደረጉን ከምክር ቤቱ አስረድተዋል።

መንግስታዊው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የፋብሪካዎቹን ግንባታ እንዲካሄድ ሃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም ግንባታዎቹን በጊዜ ገደቡ ሳያጠናቀቅ መቅረቱ በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከህንድ መንግስትና ከሌሎች አበዳሪ አካላት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዚሁ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ መበደሩም ይታወቃል።

ሃገሪቱ ስኳር ላኪ ያደርጋሉ ተብለው የታሰቡት ፋብሪካዎች ለስድስት አመት ያህል ጊዜ ባለመጠናቀቃቸውም ኢትዮጵያ በተያዘው አመት በርካታ ሚሊዮን ዶላርን በመመደብ ስኳርን ከውጭ ሃገር ለማስገባት ጥረትን እያደረገ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።

ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሆነው የስኳር ኮሮፖሬሽን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአቶ አባይ ፀሃዬ ስር ሲተዳደር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በቅርቡ ኮርፖሬሽኑ ለማስተዳደር የተሾሙ አካላት መንግስታዊው ተቋም ዘርፉ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ለኮርፖሬሽኑ ኪሳራ ግን የትኛው አካል ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ኣስካሁን ድረስ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።