በምግብ እጥረት ተጎድተው ከሚገኙት ህጻናት ውስጥ ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑት በሆስፒታል ተኝተው ክትትልን የሚፈልጉ መሆናቸው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ በከፋ የምግብ እጥረት የአካልና የጤና ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ወደ 100ሺ የሚጠጉት በሆስፒታል ተኝተው ልዩ የህክምና ክትትልን የሚፈልጉ እንደሆነ ተገለጠ።

ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ከተጋለጡ 10.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ሲሆኑ 435ሺ የሚሆኑት ደግሞ በምግብ እጥረት ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት ደርሶባቸው እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

ከእነዚሁ ህጻናት መካከልም ወደ 100ሺ የሚጠጉት በሆስፒታል ተኝተው ልዩ የህክምና ክትትልን የሚፈልጉ እንደሆነ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

ልዩ የህክምና ድጋፍን ይሻሉ የተባሉት ህጻናትም አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገላቸው ድርቁ የሚያደርሰው ጉዳት ከተጠበቀው በላይ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል።

ለተረጂዎች የሚያስፈልገው አለም አቀፍ ድጋፍ በታሰበው መጠን ሊገኝ ባለመቻሉም በሃገሪቱ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድቅ አደጋ እየተባባሰ መምጣቱንም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

ለተረጂዎች ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልግ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ክፍተት (እጥረት) መኖሩም ታውቋል።

ለተረጂዎች የሚያስፈልገው የምግብ ድጋፍ በወቅቱ ባለመቅረቡም ከ800 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ የሚል ስጋት መሆኖሩንም የእርዳታ ተቋማት አስታውቀዋል።

ከምግብ አቅርቦቱ እጥረት በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች እየደረሰ ያለውን ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋም በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን አሳድሮ እንደሚገኝም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።