ዘላለም ወርቅ አገኘሁ እስራት ተፈረደበት

ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2008)

ከእነ መምህር አብርሃ ደስታ ጋር በአሸባሪነት ተከሶ ላለፉት ሁለት አመታት ያህል በወህኒ ቤት የቆየው ዘላለም ወርቅ አገኘሁ ማክሰኞ ግንቦት 2 ፥ 2008 እስራት ተፈረደበት።

ከአንድነት፣ ሰማያዊና አረና ፓርቲ አመራሮች ጋር በሃምሌ ወር 2006 የታሰረውና ላለፉት 22 ወራት ያህል በማዕከላዊ ምርመራና በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት የቆየው ዘላለም ወርቅ አገኘሁ የግንቦት 7ትን የሽብር ዓላማ በመደገፍ በሚል ተወንጅሎ የ5 ዓመታት ከ4 ወር እስራት ተፈርዶበታል።

የአንድነት የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራቶችን ጨምሮ ሌሎች 8 ተከሳሾች ጋር በሽብተኝነት ተወንጅሎ በእስር ቤት የቆየው ዘላለም ወርቅ አገኘሁ “ደብርሃን” በተባለው ድረገጽ ላይ በተባባሪ አዘጋጅነት ሲሰራ መቆየቱም ተመልክቷል። በሌሎች ድረ-ገጾችም ላይ በኢትዮጵያ አስተያየቶቹን ይጽፍ እንደነበር ታውቋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር 2ኛ ዲግሪውን የያዘውና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እየሰራ፣ በሃገሩ ጉዳይ ላይ በጽሁፍ ሲሳተፍ መቆየቱ የተገለጸው ዘላለም ወርቅ አገኘሁ፣ ከሃምሌ 1 ቀን 2006 ጀምሮ በእስር ቤት እንደሚገኝም መረዳት ተችሏል።

ከእርሱ ጋር ታስረው የነበሩትት የሰማያዊ፣ አረና፣ እና አንድነት ፓርቲ አመራሮች የነበሩት የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ሃብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ ፍ/ቤት በነጻ እንዳሰናብታቸው ይታወሳል። ሃብታሙ አያሌው ሲለቀቅ ሌሎች ፍ/ቤት በመድፈር ተወንጅለው በወህኔ ቤት ቆይተዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋ ቢለቀቁም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ አመራት የሆነው አብርሃ ደስታ አሁንም በተጨማሪ የፍ/ቤት መድፈር ቅጣት ከእስር ቤት አልወጣም።