ግንቦት ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወኪላችን እንደገለጸው በምስራቅ ሃረርጌ ዞን በካራ ሚሊ ከተማ ትናንት በመንግስት ደጋፊ እና በመንግስት ተቃዋሚ ግለሰብ መካከል የተነሳው አለመግባባት ወደ ህዝባዊ አመጽ ተቀይሯል። የጸቡ መነሻ በከተማው ውስጥ በመሰራት ላይ ካለው መስጊድ ግንባታ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ መንግስት ያስቀመጣቸው የመስኪዱ ተወካዮች መንግስትን ከሚቃወሙት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ታወቋል። የመንግስት ደጋፊ የሆነው አቶ ሰኢዴ የተባለው ግለሰብ የመንግስትን አሰራር ይቃወማሉ የተባሉትን አቶ ጫላ የተባሉትን ግለሰብ መደብደባቸውን ተከትሎ ህዝቡ በቁጣ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ወጥቷል። ለተቃውሞ የወጣው ህዝብ በአቶ ጫላ ላይ ድብደባ በፈጸሙት አቶ ሰኢዴ ላይ እርምጃ በመውሰዱ አቶ ሰኢዴ ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ የወረዳው ፖሊስ ጣልቃ ለመግባት ሲሞክር ሃምቢሳ የሚባል የወረዳው ፖሊስ አባል በህዝቡ በተወሰደበት የመከላከል እርምጃ ህይወቱ ማለፉን ወኪላችን ገልጿል። የመንግስት ደጋፊ ናቸው የተባሉ የ3 ሰዎች መኖሪያ ቤቶችም የፈራረሱ ሲሆን፣ የወረዳው ፍርድ ቤትና የንግድ ቢሮ ጽህፈት ቤቶችም ተሰባብረው የተለያዩ እቃዎችና ፋይሎች ወድመዋል። ህዝቡ ወደ ከተማው እስር ቤት በመምራት ከ60 በላይ እስረኞች እንዲፈቱ ያደረገ ሲሆን፣ ከሃረር ከተማ የተላከው ልዩ ሃይል ጣልቃ ገብቶ ተቃውሞውን አብርዶታል። ውጥረቱ ግን እስዛሬ ቀጥሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ በግራዋና በደኖ ለወራት የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ታስረው የነበሩ ከ 1 ሺ ያላነሱ እስረኞች ዛሬ የተለቀቁ ሲሆን፣ እስረኞቹ ሃረር ከተማ ውስጥ ተገኝተው መመሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል። በእስረኞቹ ላይ ከፍተኛ መጎሳቆል እንደሚታይ የገለጸው ወኪላችን፣ አያያዛቸው አስከፊ እንደነበር ከገጽታቸው መረዳት ይችላል ብሎአል። እስረኞቹ ነገ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።