ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየአመቱ በሚያወጣቸው የሂሳብ አያያዝ መግለጫዎቹ ከፍተኛ ትርፍ እንዳገኘ ሲናገር የቆዬው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2006 እና 2007 ዓም ባሉት 2 ዓመታት ብቻ 11 ቢሊዮን 273 ሚሊዮን ብር ያላወራረደው ገንዘብ ሲኖር፣ 1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተበለሻ ብድር እንዳለው ሰነዶች አመለከቱ።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ ሰኔ 30፣ 2014 ድረስ የተለያዩ የድርጅቱ ቅርንጫፍ ባንኮች 3 ቢሊዮን 590 ሚሊዮን ከ30 ሳንቲም ፣ በ2013 ደግሞ 6 ቢሊዮን 956 ሚሊዮን ከ20 ሳንቲም ያላወራረዱት ገንዘብ መኖሩን ከንግድ ባንኩ ሰራተኞች የተገኘው የሂሳብ መዝገብ ያሳያል።
ብድር ወስደው መክፈል ያልቻሉት ድርጅቶችና ብድራቸው በተበላሸ ብድር መዝገብ ከሰፈሩት መካከል፣ ሳይጀን ዲማ ቴክስታይል ፋብሪካ 437 ሚሊዮን ብር፣ ሙሉነህ ካካ ላኪ ድርጅት 94.2 ሚሊዮን ብር፣ አኪር ግንባታ 87.1 ሚሊዮን ብር፣ ካራቱሬ እርሻ ደርጅት 55.3 ሚሊዮን ብር፣ ባዘን እርሻ እና ኢንዱስትሪ ልማት የግል ማህበር 42.1 ሚሊዮን ብር፣ የጌታ ትሬዲንግ 39.3 ሚሊዮን ብር፣ ማሜ ብረታብረት ፋብሪካ 39.2 ሚሊዮን ብር፣ የገነት ላኪና 62 ሚሊዮን ብር፣ ሸበሌ ትራነስፖርት 17.2 ሚሊዮን ብር፣ ፍጹም ዘአብ አስገዶም 14.2 ሚሊዮን ብር ቤድፋም ኢንተርናሽናል 21 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል።
ባንኩ በ2013/14 በጀት አመት 17.2 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ ቢገልጽም፣ የባንኩ ሰራተኞች እንደሚሉት ግን የተበላሸው ብድርና ያልተወረራደው ገንዘብ ግምት ውስጥ ሲገባ ባንኩ ያተረፈው ከ5 ቢሊዮን ብር አይበልጥም።