መንግስት በእስልምና ሀይማኖት ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በጊዜ ካልተገታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠረው መዘዝ ተጠያቂ ነው ሲሉ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ ሙስሊሞች ገለጡ

ህዳር 4 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት በእስልምና ሀይማኖት ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በጊዜ ካልተገታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠረው የሙስሊሞች መከፋፈልና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ ለሚያመጣው መዘዝ ተጠያቂ ነው ሲሉ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ ሙስሊሞች ገለጡ::

ኦክቶበር 30፣ በቶሮንቶ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ሙስሊሞች ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ ባወጡት መግለጫ ፤ ”  የኢትዮጵያ መንግስት በፌደራል ሚኒስትሩ ቢሮ አማካኝነትና ሕዝብ ባልወከላቸው ግለሰቦች በሚመራውና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጠቅላይ ምክር ቤት ተብሎ በሚጠራው ቡድን አስተባባሪነት፤ በጥመቱና ከእስልምና መንገድ በመልቀቁ በዓለም ባለ የሙስሊሙ ኡላማወች  የተረጋገጠበትን የአሕባሽን አመለካከት፤ የመላ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መርህ እንዲሆን የሚደረገውን ጫና በጽኑ ተቃውመዋል።”

ሙስሊሞቹ ሰፊ ወይይት ካደረጉ በሁዋላ ባወጡት መግለጫ “መንግስት በሀይማኖት ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም፣ የሙስሊሞች ጠቅላይ ጉባኤ ወይም መጅሊሱ የአህባሾች መሰባሰቢያ እንጅ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እምነት ብሶትና ፍላጎት አንጸባራቂ ባለመሆኑ መሪዎቹ ተሽረው ህዝብ በነጻ ምርጫ በመረጣቸው መሪዎች እንዲተኩ፣ መንግስት ችግር ፈጣሪ የሙስሊም ሀይሎች አሉ በሚልባቸው አካባቢዎች ከሀይማኖቱ ምሁራን፣ ከሙስሊሙ ሙያተኞች፣ እንዲሁም ከተለያዩ አገር ውስጥና ውጭ ካሉ የሙስሊም ድርጅቶችና የሙስሊም ማህበራት መሪዎች የተውጣጣ ስብሰባ እንዲጠራ” ጠይቀዋል።

መንግስት ” በሀይማኖቶች አለመቻቻል በአለም ታዋቂ ከሆነችው ሊባኖን አገር ሊቆች አመጣሁላችሁ ማለቱ ለኢትዮጵያ ሙስሊም ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ልእልና ደፋሪ ተግባር መሆኑ ታውቆ እንዲታረም እንጠይቃለን “፣ የሚሉት ሙስሊሞች፣ በአጠቃላይ የመንግስት እንቅስቃሴ የዜግነትን መብት የሚገፍ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሰካም።