ኢትዮጵያውያን በየመንና ሶሪያ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ወደ ሃገራቸው መመለስ እንዳማይፈልጉ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 28 ፥ 2008)

በመካከለኛው ምስራቅ በችግር ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዋውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን CAJ news Africa የተሰኘ ጋዜጣ ዘገበ። ባለፈው መጋቢት ወር ብቻ በጦርነት በምትናጠው ሶሪያ ችግር ውስጥ የነበሩ ከ1220 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመላቀቅ ወደመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መሄዱንም መረዳት ተችሏል።

ኢትዮጵያውያኑ ለህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ዳጎስ ያለ ገንዘብ በመክፈል ወደ የመንና ሱዳን እንደሚጓዙም ታውቋል። ሆኖም ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ለሌሎች ህገወጥ አዘዋዋሪዎች አሳልፈው እንደሚሰጡና እነዚሁ ህገወጥ አዘዋዋሪዎችም ተጨማሪ ገንዘብ ለመቀበል ሲሉ በስደተኞች ኢትዮጵያውያን አካል ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱና ለረጅም ጊዜ እንደሚያስሯቸው ለማወቅ ተችሏል።

ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ወደ የመን የገቡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ወደፈለጉት አካባቢ እንዲሄዱ እንደሚለቀቁና፣ ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ ግን ጀበል ወደሚባል ቦታ ተወስደው በአስከፊ ሁኔታ እንደሚቀመጡም CAJ news Africa የተባለው ጋዜጣ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ከስፍራው ዘግቧል።

የመን፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ የመሳሰሉ አገራት በጦርነት እየታመሱ ባለበት ሰዓት እንኳን አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በየመን ያለውን ጦርነትና፣ የሚደርስባቸውን ግፍ እንደምንም ሳይቆጥሩ አካባቢውን አቋርጠው ወደሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ይኸው CAJ news Africa የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።