በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ጎርፍ የእርዳታ አቅርቦትን አስተጓጎለ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)

በቅርቡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የጣለው ከባድ ዝናብ በአገሪቷ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የእርዳታ አሰጣጥ ሂደት እያስተጓጎለና እያወሳሰበ እንደሚገኝ ተገለጸ። የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች በጎርፉና ጭቃ ምክንያት እርዳታ ወደሚፈልጉ አካባቢዎች መሄድ እንዳልቻሉ ለመረዳት ተችሏል። በመሆኑም ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ እርዳታ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን፣ እርዳታውን ሳያገኙ ለሳምንታት ችግር ላይ ወድቀው እንደሚገኙ አሶሼይት ፕሬስ ረቡዕ አስነብቧል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ብርድ፣ የአርብቶ አደሮችን ከብቶች እየገደለ መሆኑም ተገልጿል። ከብቶችም ከድርቅ በኋላ ዝናብ ሲመታቸው ለህመምና ለሞት እንደሚዳረጉ በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮችን ዋቢ ያደረገው አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሶማሌ ክልል በተለይም በሽንሌ (ሲቲ) ዞን የተከሰተው የምግብ እጥረት ሁኔታውን ወደ ረሃብ ደረጃ እያደረሰው እንደሆነ ተገለጸ። ደሬላ ወደ ምትባል ቀበሌ ለእርዳታ የመጡ አርብቶ አደሮች፣ ሁሉም ከብቶቻቸው እንደሞቱባቸው እና በየሜዳው ወዳድቀው እንደሚገኙ  የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘጋቢ ከስፍራው ዘግቧል።

አሊ ቡር የተባሉት ኢትዮጵያዊ ከነበሯቸው 200 ከብቶች ስድስት ሲቀሩ 194 እንደሞቱባቸው ለአሶሽየትድ ፕሬስ ተናግረዋል። ከባለቤታቸውና ከ7 ልጆቻቸው ጋር በተባበሩት መንግስታት በሚተዳደረው መጠለያ የገቡት አቶ አሊ ወደመጠለያ የመጡበት ምክንያት ምግብና ውሃ እንደሚሰጥ ሰምተው እንደሆነም ተናግረዋል።