ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)
በቅርቡ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ባደረገው የማላዊ ኢምባሲ ባልደርቦች የተፈጸሙው የገንዘብ ዝርፊያ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን የማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃሙስ አስታወቀ።
ከዚሁ ዝርፊያ ጋር በተገናኘ የማላዊ መንግስት በኢትዮጵያ የማላዊ ምክትል አምባሳደር የነበሩትንና ጸሃፊውን ወደሃገሩ እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወሳል።
በኤምባሲው ልዑካኖች ተፈጽሟል የተባለን ዝርፊያ በመመርመር ላይ የሚገኘው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱ በታወቀ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ጠፍቷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከተዘረፈው ገንዘብ ግን ከ4.2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል።
የማላዊ ኢኮኖሚ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ወቅት በልዑካን አባላቱ የተፈጸመው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ሰፊ ምርመራን የሚጠይቅ እንዳልሆነ የማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አድርገው የነበሩት የዲፕሎማቲክ አባላት ገንዘቡን በተለያዩ ጊዜያት ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉት እንደነበር ማላዊ 24 የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።
ይሁንና፣ ገንዘቡ በምን ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበር ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሳይላ ፍራንሲስ ለመገናና ብዙሃን አስረድተዋል።
የተመዘበረውን ገንዘብ ለማስመለስም የማላዊ ፖሊስ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ ገልጿል።
በልዑካኑ ተመዝብብሯል የተባለው ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደፈረኖጆቹ አቆጣጠር ከ2013 እስከ 2015 አም የተፈጸመ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።