የኢትዮጵያ መንግስት ላይ በቀን ከ 1ሺ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ ይፈጸምብኛል አለ

ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)

አዲስ የኢንተርኔት አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን በህግ ለማጽደቅ በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት በየዕለቱ ከ1ሺ በላይ የሳይበር ጥቃቶችን በሃገሪቱ ይፈጸማሉ ሲል ገለጠ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብቶች የሚጻረር እንደሆነ መግለጽ መጀመራቸውን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ለመምከር ረቡዕ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ የውይይት መድረክም የተለያዩ አካላት ረቂቅ አዋጁ የግለሰብ መብቶችን ሊጋፋ የሚችል በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት ሃሳብ ማቅረባቸውም ታውቋል።

ለምርመራ ስራም ከአስፈጻሚ አካል ይልቅ በአብዛኛው የአገሪቱ ህግ ለመርማሪው አካል ትዕዛዝ መስጠት ያለበት ፍርድ ቤት እንጂ አስፈጻሚ አካል መሆን አይገባውም ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መርጃ ለመረዳት ተችሏል።

በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው ረቂቅ በአዋጅ ግለሰቦች በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ወንጀል እንዲመሰረትባቸው የሚያደርግ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ሰፍሯል።

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ረቂቅ አዋጁ ከጸረ-ሽብርተኛ አዋጁ ህጉ በባሰ መልኩ የዜጎችን ነጻነት የሚጋፋ ነው ሲሉ ተቃውሞን እያቀረቡ ይገኛሉ።

በየዕለቱ ከአንድ ሺ በላይ የሳይበር ጥቃቶችን በሃገሪቱ እንደሚፈጽሙ ያስታወቀው የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በበኩሉ ድርጊቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ህጉን ማፅደቁ አስፈላጊ ሆኖ መታመኑን ገልጸዋል።

በኤጀንሲው የህግና ፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ካሳ፣ የሳይበር ጥቃቶቹ የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል።

ይሁንና፣ በየዕለቱ ይፈጸማሉ የተባሉት የሳይበር ጥቃቶች በማን አካል የሚፈጸም እንደሆነ ዝርዝር መረጃን ያልጠሰጠ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ በቅርቡ ህግ ሆኖ ይጸድቃል ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብን በመመደብ ከአንድ የጣሊያን ኩባንያ የረቀቁ የኢንተርኔት የስለላ ተግባርን ለመፈጸም የሚረዱ ቁሳቁሶችን ሲቀበል መቆየቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይሁንኑ አገልግሎት የግለሰብ እንዲሁም የጋዜጠኞችንና የፖለቲካ አመራሮችን የግል ስልኮችንንና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ለመሰለል ሲጠቀም መቆየቱም በተለያዩ አካላት ይፋል መደረጉ ይታወቃል።

ይሁንና፣ መንግስት በተቃራኒው የሳይበር ጥቃት ሰለባ እየሆነ መምጣቱን በመግለፅ አዲስ አዋጅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ይገልጻል።