ሚያዚያ ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ቁጥር 652 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ተላልፈሀል ተብሎ ነው የሽብር ክስ የተመሰረተበት፡፡
የአቶ ዮናታን ክስ፤ ትናንት ሚያዝያ 26/2008 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዳኞች ቢሮ በንባብ ተሰምቷል።
በንባብ በተሰማው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ አቶ ዮናታን የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24/2008 ዓ.ም ጀምሮ በሚጠቀምበት ድረ-ገጽ በተለይም በፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ‹‹አመጽና ብጥብጥ›› ለማስቀጠል የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን፤ ማለትም የኦነግን አላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ይላል።
አቃቤ ህግ በቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ላይ ለመሰረተው ክስ ዝርዝር ማስረጃ አድርጎ በማያያዝ ያቀረባቸው አቶ ዮናታን በግሉ የፌስቡክ አካውንት የለጠፋቸውን ፅሁፎች ናቸው፡፡
ወጣት ዮናታን፦ ‹የኦነግን አላማ ለማሳካት፤ አመጽና ብጥብጡ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት በማሰብ በሚጠቀምበት ፌስቡክ ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመጻፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በማዘጋጀት፣ በማሴር፣ እና በማነሳሳት ወንጀል› መከሰሱን የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል፡፡
አቃቤ ህግ እንደ ማስረጃ ክሱ ጋር ካያያዛቸው የዮናታን ጽሁፎች መካከል፦ በቀን 08/04/2008 ዓ.ም፦ “ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም” የሚለውና ስለመንገድ መዝጋት የጻፈው፣ እንዲሁም በ11/04/2008 ዓ.ም “ኢህአዴግ ችግርን ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም” በሚል ርዕስ የጻፈው ይገኙበታል።
ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰው ለብቻው በተከፈተ ፋይል ሲሆን፣ ትናንት ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ጉዳዩ በቢሮ እንዲታይ በመደረጉ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በችሎቱ መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በመጨረሻም ዳኞቹ ዮናታን ተስፋዬ የክስ መቃወሚያውን ይዞ ለመጪው ግንቦት 15/2008 ዓ.ም እንዲቀርብ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡