ሚያዚያ ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ ውስጥ የፀረ ሽብር ሕግን ከለላ በማድረግ መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጎችን ማሰር፣ መግደልና ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም ተጠናክሮ መቀጠሉን የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ ገልጿል። ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት የቀጠፈው ዘግናኝ እልቂት በህወሃት ኢህአዴግ መራሹ ገዥ ቡድን የተቀነባበረ መሆኑን አስታውቋል።
ይህን ኢሰብዓዊ እልቂት ተቃውመው ለመብታቸው የታገሉት ከ 22 በላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የሃሰት ክስ እንደተመሰረተባቸው አመልክቶ ፣ በህወሃት የተቀነባበረ ሴራ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ካለ ፍትሕ በእስር ቤት እየማቀቁ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ ያለው የፀረ ሽብር ሕግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በሚጻረር መልኩ የወጣ ሲሆን ይህም የዜጎችን የመጻፍ፣ የመናገርና የመቃወም ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በሚጥስ መልኩ ሆን ተብሎ ተረቆ በሥራ ላይ መዋሉን አስታውቋል።
በኦሮሚያ የተነሳውን ሰላማዊ የዜጎችን ጥያቄ በመደገፍ ከሕዝባቸው ጋር በመሆን ሲቃወሙ ከነበሩት ውስጥ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የፓርቲው ፀሃፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ አቡላና ሌሎችም በፈጠራ የሽብር ክስ መከሰሳቸውንና የመብት ጥሰቱ ተባብሶ መቀጠሉን ሪፖርቱ አመላክቷል።
መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በሽብር ሕግ ስም አላግባብ ታስረው የሚገኙ ንጹሃን ኢትዮዮጵያዊያንን ህወሃት መራሹ መንግስት ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታዎች ክሳቸውን በማንሳት ሊፈታቸው ይገባል ብሎአል።