ሚያዚያ ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሙረሌ ጎሳ ሚሊሺያዎች ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓም ከጋምቤላ ተጠልፈው ወደ ደቡብ ሱዳን ከተወሰዱት ከ125 ህጻናት እና ሴቶች መካከል 32 ቱ መገኘታቸውን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
አሶሼትድ ፕሬስ የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ ኦጋቶ ቻንን በመጥቀስ እንደዘገበው ፣ የአካባቢው የጎሳ አባላት ህጻናቱን የሰበሰቡት በሊኩአንጎሌ ወረዳ በሚገኙ ሶስት መንደሮች ነው። የተገኙት ህጻናት ወደ ዋና ከተማዋ ፒቦር ከተወሰዱ በሁዋላ ወደ ኢትዮጵያ ይላካሉ። የአካባቢው የጎሳ መሪዎች ሌሎችን ህጻናት በመፈለግ ላይ መሆናቸውም በዘገባው ተመልክቷል። የህጻናቱ መገኘት ይፋ ቢደረግም ከወላጆቻቸው ጋር ስለሚገናኙበት ቀን የተባለ ነገር የለም።
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጋትሉክ ቱት ተገኙ ስለተባሉት ህጻናት ምንም መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።
የሙርሌ ጎሳ ሚሊሺያዎች በኢትዮጵያ ኑዌሮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ230 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል። መንግስት የታገቱትን ለማስለቀቅ ከበባ ማድረጉን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ ዘግይቶ ግን ችግሩን በድርድር ለመፍታት ጥረት መጀመሩን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች ገልጿል።