ሚያዚያ ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ200 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን እና ከ108 በላይ ህጻናትና ሴቶች በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት የተጠለፉበትን አስደንጋጭ ዜና ተከትሎ መንግስት በሰጠው መግለጫ፣ የተጠለፉ ሰዎችን ለማስመለስ መከላከያ ሰራዊቱ ወደ ሱዳን ድንበር ዘልቆ መግባቱንና ከበባ ማካሄዱን በተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ ቢቆይም፣ ሰዎቹ ከተጠለፉ ከሁለት ሳምንት በሁዋላ፣ ከጠላፊዎቹ ጋር ድርድር በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል። የኢህአዴግ መንግስት ከደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከነዋሪዎች ጋር እየተደራደረ መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ሳያስታውቅ፣ ለውጭ አገር መንግስታት ገለጻ መስጠቱ፣ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወይስ ለውጭ መንግስታት ነው የሚል ጥያቄ አስነስቶበታል። ከሚያዚያ 7 በሁዋላ ባሉት ሁለት ቀናት ከተሰጠው መግለጫ ውጭ፣ ሰዎቹን የማስለቀቅ ጥረቱ ስለተደረሰበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ ያልተሰጠ ሲሆን፣ አዳዲስ መረጃ የሚጠይቁ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መለስ የሚሰጣቸው የመንግስት ባለስልጣናት ማጣታቸውን ተከትሎ እለታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ለማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
የኢህአዴግ መንግስት ሰዎቹን ወታደራዊ ሃይል በመጠቀም ለማስለቀቅ የነበረውን እቅድ ለምን እንደሰረዘ የገለጸው ነገር የለም። ምንም እንኳ ሰዎቹ በድርድር መለቀቃቸው የተሻለው አማራጭ መሆኑ ቢታወቅም፣ ድርድሩ ረጅም ጊዜ መውሰዱ በታጋቾችና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ መንግስት የራሱን ምስል ለመገንባት “ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ስራዬን አድንቁልኝ” የሚል ስብሰባ ማዘጋጃቱ፣ በሰዎች ስቃይ፣ የራስን ገጽታ ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ይመስላል” ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።