በጋምቤላ ክልል አዲስ ግጭት ተቀሰቀሰ

ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2008)

ከ200ሺ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በሚገኙበት የጋምቤላ ክልል የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ግጭት በአዲስ መልክ መቀጣጠሉ ተገለጸ። ይኸው ግጭት በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን አስጠልሎ በሚገኝበት የጃዊ መጠለያ ጣቢያ መቀጠሉንና በድርጊቱ ተጨማሪ ሰዎች ይሞታሉ የሚል ስጋት መኖሩን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ከ10 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ግድያ ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውን 45 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ሃሙስ አስታውቀዋል።

በሁለት የስደተኛ ልጆች በተሽከርካሪ አደጋ መገደልን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ይኸው ግጭት ከ270 ሺ በላይ በሚሆኑት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መካከል የጎሳ ግጭትን ሊያባብስ ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የጸጥታ ሃይሎችን በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎቹ ዙሪያ አሰማርቶ ቢገኝም ግጭቱ በአዲስ መልክ በጃዊ መጠለያ ጣቢያ መቀጠሉን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

በስደተኞቹ መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት እልባት ለመስጠትም በመንግስት ተወካዮች በኩል ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትሉክ ቱት ገልጸዋል።

በሁለቱ ስደተኞች ህጻናት መገደል ቅር የተሰኙ የኑዌር ተወላጆች 14 ኢትዮጵያውያንን በመግደል ሌሎች የመጠለያ ጣቢያ ሰዎችንም እንደጎዱ ተገልጿል።

በህጻናት ሞት ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት መልኩን በመቀየር በመጠለያ ጣቢያ በሚገኙ ጎሳዎች መካከል አለመግባባትና ግጭትን ፈጥሮ እንደሚገኝም ከሃገር ኢት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በክልሉ የተፈጠረው ውጥረት ተከትሎም በጋምቤላ ከተማ ያልተለመደ የጸጥታ ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

ከ10 ቀናት በፊት ከ200 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ግድያ ምክንያት የሆነ ጥቃት በክልሉ ተጨማሪ ውጥረትን አንግሶ የሚገኝ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ግጭቱ ተባብሱ እንዳይቀጥልም ሁሉም ወገኖች መግባባትን እንደሚያደርጉ አሳስቧል።